የገቢዎች ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት 198.1 ቢሊየን ብር ሰበሰበ

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት 198 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2011 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምንና የ2012 በጀት አመት እቅድን በማስመለከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመግለጫው ላይ በ2011 በጀት ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅዶለት ከነበረው 213 ቢሊየን ብር ውስጥ 198 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ምንም እንኳ ከእቅዱ አንፃር ዝቅ ቢልም ከ2010 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ22 ቢሊየን ብር ብልጫ ወይም የ12 በመቶ እድገት ማሳየቱን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ ያልተሳካበት ምክንያት በዋነኝነት የሀገሪቱ አለመረጋጋት እንደሆነ ሚኒስትሯ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ የሀገር ውስጥ ገቢ ድርሻ 120 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር (61 በመቶ) ሲኖረው፣ ከቀረጥ የተሰበሰበው ገቢ ድርሻ ደግሞ 77 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር (39 በመቶ) እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ በ2012 በጀት ዓመት በፓርላማ እንዲሰበሰብ የፀደቀለት የገቢ ዕቅድ 224 ቢሊየን ብር ሲሆን ይህን ዕቅድ በማስፋት ከሀገር ውስጥ ገቢ150 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ከጉምሩክ ደግሞ 98 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጥቅሉ 248 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ወደ ተግባር መግባቱ ተነግሯል፡፡