3ኛ ወገን የመድን ሽፋን የሌላቸው ተሽከርካሪ ባለቤቶች ሕጋዊ እንዲሆኑ ኤጀንሲው አስጠነቀቀ

የሶስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሌላቸው ተሸከርካሪ ባለቤቶች ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስጠነቀቀ፡፡

ኤጀንሲው ለአንድ ወር የሚቆይ የመድን ሽፋን ንቅናቄ ከሐምሌ 10 ቀን እስከ ነሐሴ 10/ 2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚያካሂድ ገልጿል፡፡

በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ መጠቀም የማይችሉ ባለቤቶች ከ3ሺህ እስከ 5ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት አልያም እስከ 2 ዓመት የሚደርስ እስር ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙት ተሸከርካሪዎች ከ1 ሚሊየን በላይ ቢሆኑም 3ኛ ወገን የመድን ሽፋን ያላቸው ተሸከርካሪዎች ቁጥር 569 ሺህ ብቻ በመሆኑ ግማሽ አካባቢ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ያለ 3ኛ ወገን የመድን ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

የተሸካርካሪ አደጋ 3ኛ ወገን መድን ሽፋን ለተሸከርካሪ ባለቤቶች አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅት ላደረሱት የንብረትም ሆነ የሰው አካል ጉዳትና ሞት ያለምንም ችግር ተጎጂዎችን ለማሳከምና እንደጉዳታቸው መጠንም ካሳ ለመክፈል የሚስችላቸው የመድን ሽፋን ነው፡፡