በመጪው ሐምሌ 22 በአራቱ ክልሎች ብቻ 291 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ

በመጪው ሐምሌ 22  በአገር አቀፍ በሚኖረው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በአራቱ ክልሎች ብቻ 291 ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ ተገለጸ፡፡

ችግኞቹ የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ለማሳካት የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የትግራይና የደቡብ ክልሎች ይተከላል ነው የተባለው፡፡

“አረንጓዴ አሻራ” በሚል መሪ ሀሳብ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘው ዕቅድ አራቱ ክልሎች 291 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ማቀዳቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ለመትከል የታቀደ ቢሆንም፤ አራቱ ክልሎች ከታቀደው በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልል ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 126 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና ለዚህም ለችግኝ መትከያ 106 ቦታዎች እና 53 የሚጠበቁ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡

ምስራቅ ሸዋ፣ ኢሉባቡር፣ ጅማ፣ አርሲ እና ምዕራብ ሸዋ በክልሉ የተለዩ ችግኙ የሚተከልባቸው ዞኖች ናቸው ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል 108 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ ለችግኝ ተከላው 64 የተለዩ ቦታዎች እና 40 የሚጠበቁ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው በመረጃው ተመልክቷል፡፡

ችግኞቹ በባህርዳር፣ ሰሜን ሸዋ(ጣርማበር)፣ ሰሜን ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር(ሶስት ስፍራዎች)፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ(ተንታ) ዞኖች የሚተከሉ ይሆናልም ነው የተባለው።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 48 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ በክልሉ ለሚተከለው ችግኝ ስድስት ቦታዎች እና 21 የሚጠበቁ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል።

ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ሲዳማ እና አርባ ምንጭ ደግሞ ለችግኝ ተከላው የተለዩ ዞኖች ናቸው።

በትግራይ ክልል ዘጠኝ ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ አምስት የሚጠበቁ ስፍራዎች ለችግኝ ተከላው መዘጋጀታቸው ታውቋል።

ችግኞቹም በመቐለ፣ አድዋ፣ ሽሬ፣ አዲግራትና ማይጨው ዞኖች እንደሚተከሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአራት ቢሊየን ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር እስካሁን ከ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን የችግኝ ተከላው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።

በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም አራት ቢሊየን ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደው ተከላም የዚሁ መርሃ-ግብር አካል መሆኑ ይታወቃል።