የአውሮፓ ኀብረት ለኢትዮጵያ 36 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት ተፈራረመ

የአውሮፓ ኀብረት በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በበጀት ለመደገፍ የሚያስችለውን የ36 ሚሊዮን ዮሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ።

የኀብረቱ የድጋፍ ስምምነት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና የከባቢ አየር በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እንዲሁም የመንግስትን መዋቅር ለመደገፍ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴና በኀብረቱ የዓለም አቀፍ ልማትና ትብብር ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ ፈርመዋል።

ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አውሮጳና ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ቅነሳ ያላቸው የትብብር ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ነው።

ኀብረቱ ላለፉት አስር ዓመታት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለተያያዙ መርሐ ግብሮች 400 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።

”ኢትዮጵያ የነደፈችውን የልማት ግብ ስኬታማ ለማድረግ በአየር ንብረትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚከወኑ ተግባራት ወሳኝ ናቸው” ብለዋል ኮሚሽነሩ።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ተግባራት ላይ የሚከናወኑ ስራዎች ለአጠቃላይ  ልማትና ለዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሁም ለፓሪሱ ስምምነት ስኬታማነት ወሳኝ ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በአውሮፓ ኀብረት በኩል የተደረገው ድጋፍም ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዙሪያ የጀመረችውን ተግባር ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

በኀብረቱ በተደረገው ድጋፍ የሚከወነው መርሃ ግብር እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ2019 እስከ 2022 የሚዘልቅ ነው።