የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረምን ከመስከረም 12 እስከ 14/2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የኢንስትመንት አማራጮችን ለአለም ስለሚያስተዋዉቅ ሚናው የጎላ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ፎረሙ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2014 እና15 በኢትዮጵያ ለሁለት ጊዜ ተካሄዷል፡፡

ፎረሙ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በአንድ የሚያሰባስብና የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያስፋፋ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

ፎረሙ በቱሪዝም ኢትዮጵያ በቤንች ኢቨንትስ እና በካሊብራ ሆቴል አማካሪዎች አስተባባሪነት የሚካሄድ ነው፡፡

ይህ መድረክ የሀገሪቱን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንዲሁም አቅም ያላቸውን የዘርፉ ባለሀብቶችን ለመሳብ አጋዥ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የቱሪዝም ኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ሌንሳ መኮንን በፎረሙ የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎችና የተለያዩ የቱሪዝምና የሆቴል አገልግሎቶችን የሚያስተዋዉቀዉ፤ ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስጎብኘት እንዲሁም ሌሎች ተያያዝ ክንውኖች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ስራ አስፈጻሚዋ የገለጹት፡፡

በርካታ አለም አቀፍ ሆቴሎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትና ላሉትም የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ መሰል ፎረሞች ሚናቸው የጎላ መሆኑን በመረዳት እነዚህ መድረኮች በሀገር ውስጥ እንዲካሄዱ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ የካሊብራ ሆቴል አማካሪዎች አስታውቋል፡፡

የአማካሪ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ነዋይ ብርሀኑ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያገኙበትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የዕውቀት ሽግግርን የሚያረጋግጡበት እንዲሁም ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የበኩላቸውን ለመወጣት ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቤንች ኢቨንትስ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ማቲው  ዌሂስ በመድረኩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የዘርፉ አመራሮች ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ተቁመዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅና አለም አቀፍ ድርጅቶችን ለመሳብ በር የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መሰል መድረኮችን በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እንደሚያካሂዱ የገለጹት ስራ አስኪያጁ ለሶስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ፎረም በተለያዩ የፓናል ውይይቶች ኤግዝቢሽኖችና ወርክሾፖች እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡