የኢትዮጵያ የቡና ምርት መለያን በዓለም ማስተዋወቅ ሊጀመር ነው

የኢትዮጵያን የቡና የምርት መለያ /ብራንድ/ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።

የኢትዮጵያን የቡና ምርት መለያ /ብራንድ/ በተመለከተ ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።

ና የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የብራንድ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ምንሊክ ሀብቱ እንዳሉት ÷ከአሁን ቀደም የኢትዮጵያን ቡና በዓለም የሚያስተዋወቅ አንድ መልክ ወይም ገጽ አልነበረም።

የሐረር፣ ሲዳሞና ይርጋጨፌ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢመዘገቡም እንደ ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን ቡና የሚያስተዋውቅ አገራዊ የቡና የምርት መለያ አለመኖሩ ችግር እንደፈጠረ አንስተዋል።

ከኢትዮጵያ የቡና ምርት ጥራት ያነሰ ያላቸው አገራት ብራንዳቸውን አጉልተው በማስተዋወቅ በተሻለ ዋጋ ቡናቸውን እየሸጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሌሎች አገራት የሚያዘጋጇቸው የምርት መለያዎች በሰው አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋና የማይረሳ እንደሆነ ገልጸው ከዚህም አኳያ የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክ ተጠቅማ የቡና ምርት መለያ ብራንድ ሊኖራት ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የቡና ምርት የሚያስተዋወቅ መለያ በማስፈለጉ ከአንድ ዓመት በላይ በወሰደ ጊዜ ብራንድ እንደተዘጋጀ አቶ ምንሊክ ጠቅሰዋል።

አክለውም ብራንዱን በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት፣ በዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤትና በሌሎች አገራት የማስመዝገብ ስራ በቀጣይ እንደሚከናወን  ገልፀዋል።

ብራንዱን ከማስመዝገብ ጎን ለጎንም በጃፓን ርዕሰ መዲና ቶኪዮ ከመስከረም 1 እስከ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የልዩ ጣዕም ቡና አውደ ርዕይና ጉባኤ ላይ በይፋ እንደሚተዋወቅ ነው የተናገሩት።