የፌዴራል ፖሊስ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

የፌዴራል ፖሊስ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሙስና ጨርሶ እንዳይፈፀም በጋራ ለመከላከልና ተፈፅሞም ሲገኝ ለመመርመር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ በዋናነት የተደራጀ የፀረ ሙስና ዘመቻ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በተለይም በአገሪቱ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሆነ የሙስና ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል ስምምነት መሆኑም ተገልጿል፡፡

ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው አገራዊ ጥረት ሶስቱም ተቋማት ተጠናክረው ተግባሩን በጋራ ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡

የምርመራውን ስራ ፌዴራል ፖሊስ፣ የመክሰሱን ስራ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንዲሁም ሙስናን የመከላከሉንና የማስተማሩን ስራ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደሚሰሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህንኑ በቅንጅት ለመስራት ነው ስምምነቱ የተፈረመው፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመከላከል ደክሟል በሚል በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሳውን ቅሬታ በማስተካከል በቀጣይ ሙስናን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል የሚያስችል ስራ እያከናወነ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡