ሊድ አሲድ ለአካባቢ አየር ንብረት ለዉጥ የሚያበረክተዉን አስተዋፅኦ ለመቀነስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ዉይይት ተካሄደ

ባገለገሉ ባትሪዎች ዉስጥ የሚገኘዉ ሊድ አሲድ ለአካባቢ አየር ንብረት የሚያበረክተዉን አስተዋፅኦ ለመቀነስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ዉይይት ተካሄደ፡፡

በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለዉጥ ኮሚሽን የፖሊሲ ፤ ደረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ጀነራል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አየለ ሄገና በዉይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት 30 አመታት የአየር ንብረት ለዉጥን ተፅዕኖ ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን ስታከናዉን ቆይታለች፡፡

ባለፉት 2 አመታትም የተለያዩ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዲደረግባዉ መደረጉን አዉስተዉ በቀጣይ ወደተግባር ለሚገባዉ የፍኖተ ካርታ ዝግጅት መንግስት የበኩሉን እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡

የሊድ አሲድ በአለም አቀፍ ደረጃ 977 ቢሊየን ዶላር በማሳጣት ተፅዕኖ እንደሚያደርስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአፍሪካም 134.7 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ጉዳት ማድረሱንና ይህም በአህጉሩ 4 በመቶ ለሚሆነዉ የምርት መቀነስ ምክኒያት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይህ አሲድ በኢትዮጵያም 4 በመቶ ሃገራዊ ምርት እንዲቀንስ የበኩሉን አስተዋጾ ማበርከቱ ተነግሯል፡፡

ፍኖተ ካርታዉ በመጀመሪያ ዙር 1.1 ሚሊየን ዩሮ ከባለድርሻ አካላት ተመድቦለት ወደተግባር እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

በዉይይቱ ላይ የአዉሮፓ ህብረት፤ በሃይል አቅርቦት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡