ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ላይ ያሳዩትን ህብረት በሁሉም መስክ እንዲደግሙ ተጠየቀ

ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ላይ ያሳዩትን ህብረት በሁሉም መስክ እንዲደግሙ ተጠየቀ፡፡

የ2011 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃግብር የማጠቃለያ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በብሔራዊ ቤተመንግስት ተካሂዷል፡፡  

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ላይ የታየዉ ኢትዮጵያዊ ህብረትና ተሳትፎ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም መስክ ላይ ከተባበሩ የማያስመዘግቡት ድል ላለመኖሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መረሃግብር ከታቀደለት በላይ ስኬታማ እንደነበርም ፕሬዝዳንቷ ጠቁመዋል፡፡

በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው የ2011 የችግኝ ተከላ መርሃግብር የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ በርካታ አርቲስቶች ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

እንዲሁም ብሔራዊ አንድነት ጎልቶ በተስተዋለበት በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞች በተተከሉበት የሐምሌ 22ቱ ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃግብር በየክልሉ ተሰማርተው የነበሩ የአርቲስቶች ቡድን ከየክልሉ ይዘው የመጡትን ምልዕክት በማስተላለፍ ዘጠኙን ክልሎችንና ሁለት ከተማ አስተዳደሮችን የሚወክሉ አንዳንድ ችግኝ በቤተመንግስት ውስጥ ተክለዋል፡፡

ክልሎቹንና ከተማ አስተዳደሮቹን ወክለው ከተተከሉ 11 ችግኞች በተጨማሪ በመሃከላቸው የኢትዮጵያ አንድነትን የሚወክል 12ኛው ችግኝ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን በመወከል ተተክሎ የመርሃግብሩ ማጠቃለያ ተደርጓል፡፡