የጃፓን ባለሃብቶች በአፍሪካ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ 20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርገዋል-ሽንዞ  አቤ

የጃፓን ባለሃብቶች በአፍሪካ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ 20 ቢሊዮን ዶላር በላይ  ኢንቨስት አድርገዋል-ሽንዞ  አቤ፣

7ኛው የቶኪዮ ለአፍሪካ ልማት /ቲካድ/ ጉባኤ በጃፓን ዮኮሃማ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ  አቤ፣ የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጎቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሃማት፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከታደሙት መካከል ናቸው ።

እየተካሄደ ባለው 7ኛው የቶኪዮ ለአፍሪካ ልማት /ቲካድ/ ጉባኤ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤ ባደረጉት ንግግ፤ ባለፉት ዓመታት የጃፓን የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች በአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ 25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ መዋዕለንዋያቸውን አፍስሰዋል ብለዋል፡፡

የጃፓን ባለሀብቶች በአፍሪካ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለሃብቶቹ በባለፉት ሶስት ዓመታ ብቻ እንኳ ወደ 20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት እንዳደረጉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ፣ በሱዳን እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የታየውን ሰላም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የግብጽ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው የቲካድ መሪ ቃል አፍሪካ በቴክኖሎጂ እና ሰው ሀይል በኩል ያሉባትን ክፍተቶች የለየ መሆኑ ለቀጣይ ስራ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ጃፓን በአፍሪካ 3 ሚሊየን የሚደርሱ ህፃናት መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻሏንና ይህም የጃፓን መንግስት በአህጉሩ ላይ የልማት ውጤት እንዲመጣ ያሳየ ተነሳሽነት ነው ብለዋል፡፡

ጃፖንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአፍሪካ በስፋት ሊሰማሩ ይገባል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በበኩላቸው በአፍሪካ ሀገራት የተፈረመው ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት የንግድ ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ገልጸው፣ ጃፓን በአፍሪካ ላይ እያደረገች ያለውን ፍላጎት ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በ3 ቀናት ቆይታው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የተወያዩበትን የዮካሃማ 2019 ስምምነት መሪዎችም ተወያይተው ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው በህዝብ አስተዳደር፣ በኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአፍሪካ ልማት ላይ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ትኩረት አድሮጎ የሚወያይ ሲሆን፤ በአፍሪካና በጃፓን የንግድ ግንኙነት ምን መሆን ባለበት ሁኔታም ይመክራል ተብሏል።