በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ሊተገበር ነው

ኢትዮጵያ በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስራ ተግባራዊ ልታደርግ ነው፡፡

የአረንጓዴ ልማት ስራው “ስዊች  አፍሪካ ግሪን” ከተባለ ተቋም ጋር በትብብር የሚሰራ  ሲሆን የገንዘቡ ምንጭ የአውሮፓ ህብረት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በስድስት የአፍሪካ ሀገራት የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ሲያከናውን መቆየቱን ነው ‘ስዊች አፍሪካን ግሪን’ የተባለው ተቋም ያስታወቀው፡፡

ተቋሙ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ በግብርና፣ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ በኢንዱስትሪ እንዱሁም ቱሪዝም ዘርፎች  የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም የአረንጓዴ ልማት ስራን በሰፊው ስታከናውን መቆየቷ ያስታወሱት የአካባቢ፣ የደን እና የአየር ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ፤ ከመሰል ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት  የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ተወካይ የሆኑት ኤሪክ ሐበርስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ለሌሎች ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡

‘ስዊች አፍሪካን ግሪን’ የተባለው ተቋም ከሁለት አመታት በፊት በጋና የተመሰረተ ሲሆን፤  ጋና፣ ሞሪሺየስ፣ ኬንያና ዩጋንዳ ፕሮጀክቱን በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡

በታሪኳ መንግስተአብ