ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና ልኡካቸው ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ልኡካቸው የኢንቨስትመንት እድሎችንና ጅማሮዎችን ማበረታታትን በተመለከተ ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር ተወያዩ፡፡

የመጀመሪያው ውይይት ከጃፓን የውጪ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ) ሊቀመንበር ጋር ያካሄዱ ሲሆን፣  ጄትሮ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያደረገች ላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋፋትና ቀጣናዊ ውህደትን በሚያበረታታው የመደመር እሳቤ መሰረት የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችን ለመርዳት እንዲነሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጎአድራጊና በሳሳካዋ አፍሪካ ስር የኢትጵያን የግብርና ዘርፍ ድጋፍን የሚመራውን የኒፖን ፋውንዴሽን ሊቀመንበር የሆኑትን ዮሄ ሳሳካዋን አነጋግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ጃፓን ካላት የተፋሰስ ወንዞችን ማጽዳት ስኬት በመነሳት የአዲስ አበባ ወንዞችን የማጽዳትና የከተማ ግብርና ልማት ዙሪያ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ ሰላምን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት በነበራቸው ውይይት ወቅት አድንቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ቅድሚያ የሚሳጣቸውን በማጉላት ጃይካ እነዚህኑ የትኩረት አቅጣጫዎች በማሳካት፣ በሰው ኃብትና ኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ነው፡፡