በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ትላልቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ

አመታዊው የአምባሳደሮች ስብሰባ “ተቋማዊ ለውጥ ለላቀ ዲፕሎማሲ” በሚል መሪ ሀሳብ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የተመለከተ ሪፖርት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ  አቅርበዋል።

በበጀት አመቱ በርካታ ትላልቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን በዚሁ ሪፖርት አንስተዋል።

የተወሰኑት በቀጣይ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ ለልማት የሚውል ገንዘብ በተሻለ ደረጃ እንደተገኘ ያብራሩት ሚኒስትር ዲኤታዋ ፤ አዲሱ የኢንቨስትመንት ፖሊሲማሻሻያ በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለፁት፡፡

የዲያስፖራ የልማት ተሳትፎም ሌላው በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝና የራሱ አደረጃጀት እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለቀጣይ ስድስት ቀናት በሚቆየው በዚህ አመታዊ የምክክር መድረክ  በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን  በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

በስብሰባው በውጭ ሀገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮችና የቆንስላ ጄነራሎች ተሳትፈዋል።