በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 26 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 26 ሽጉጦች ቦምባስ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ትናንት ከምሽቱ 3፡00 አካባቢ  በጉምሩክ ፈታሾችና በፌዴራል ፖሊስ አማካኝነት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በወቅቱ ከሽጉጦቹ ጋር ሁለት የሽጉጥ ሰደፍና 11 ካርታ የተያዘ ሲሆን፤ ህገ-ወጥ መሳሪያው ኮድ3-30513 የሰሌዳ ቁጥር ባለው አይሱዙ ተሸከርካሪ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡

ኮንትሮባንድ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ያስከትላል ያለው የገቢዎች ሚኒስቴር ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የህዝብ ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል ብሏል፡፡

የጥቂት ህገ-ወጦች ፍላጎት በሚያሟላው የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ምክንያት የሀገር ሰላም እንዳይደፈርስ የሰላም ባለቤት የሆነው ህዝብ በንቃት እንዲጠብቅ የገቢዎች ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡