በደቡብ አፍሪካ  የሚስተዋለውን ጥቃት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት በውይይት ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ተባለ

በደቡብ አፍሪካ በሌሎች ሀገር ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ያነጣጠረ ባይሆንም በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ተወያይተው መፍትሄ እንደሚፈልጉ ኘሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አባላቱ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዳሰጋቸውና ከመንግስት ጋር ውይይት አድርገው መፍትሄ እንዲፈልጉላቸው ጠይቀዋል።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በ28ኛው የዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ያሉት ፕሬዚዳንቷ ከዚህ ጎን ለጎን ነው ከኢትዮጵያውያኑ ጋር የተወያዩት።

ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በጉባኤው ላይም በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እና በሰላም ዙሪያ ባተኮረው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።

ፕሬዚደንቷ የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ ከፖሊሲ ማውጣት እና ከአዳራሽ ውስጥ ውይይት ባለፈ ታች ድረስ ወደ ህዝቡ ወርዶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ወጣቶች በስደት ለሚኖሩበት ሀገር እንደ ስጋት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦም እንዳላቸው መታየት እንዳለበት ገልጸዋል።

በሰላም መፍትሄ አመንጪነት ዙሪያ ሴቶችም በሀላፊነት ደረጃ ሊሳተፉ እንደሚገባ ፕሬዚደንቷ ጠቁመዋል።

እንደ ፕሬዚደንቷ አገላለጽ የልማት ጉዳይ እና የሰላም አጀንዳዎች ተነጣጥለው የሚታዩ መሆን የለባቸውም።

ምንጭ፦ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት