የወጪ ንግድ ኮንትራት ክህደት በሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ መሆኑ ተገለጸ

የወጪ ንግድ ኮንትራት ክህደት በሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው።

የወጪ ንግድ ኮንትራት ክህደት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ፈቃድ እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በ2012 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የሀገሪቱን አቅም መነሻ ያደረገ እቅድ አዘጋጅቶ እና የቁጥጥርና አመራር ስርዓት ዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናግረዋል፡፡

በሚኖረው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በትክክል  የተቀመጠውን ህጋዊ አሰራር ተከትለው የሚሰሩ ነጋዴዎችን በመለየትና በመደገፍ ጥረት እንደሚደረግ የተመለከተ ሲሆን፤ በህገ-ወጥ ተግባር ተሰማርተው በተገኙት እና የገቡትን የኮንትራት ውል በሚክዱ ነጋዴዎች  ላይ የንግድ ፈቃድ እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

ሚኒስቴር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ በተያዘው በጀት ዓመት የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር፣ ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመከላከል እንዲሁም የወጪ ንግድ ምርቶች የግብይት ማዕከላትን አሰራር በማቀላጠፍ ህጋዊ ለሆነው የንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል፡፡

በተለይ በአስገዳጅነት በምርት ገበያ የሚያልፉ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ ቀይ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ እና ኑግ ምርቶች የኮንትራት አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶላቸው ነጋዴዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በሚሆኑበት አሰራር ውስጥ እንዲያልፉ ይደረጋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የገንዘብ ትርፍ ከማግኘት በተጨማሪ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚሰሩ መሆኑን አውቀው በታማኝነት መስራት እንዳለባቸውም መናገራቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።