አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ቀልጣፋና በቂ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን የቄራዎች ድርጅት አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ ቄራዎች ድርጅት የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና በቂ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

ዝግጅቱን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የቄራዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል፤ ድርጅቱ በቀን በአማካኝ ከ1600 በላይ ከብቶችና እስከ 1500 የሚሆኑ በግና ፍየሎች የእርድ አገልግሎት የመስጠት አቅም ያለ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ በበዓላት  እስከ 5000 እንስሳት የእርድ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡

በአዲሱ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ እስከ 3000 ከብቶችና 2000 በግና ፍየሎች የእርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ግን ድርጅቱ ህገወጥ የእርድ አገልግሎቶች ፈተና እንደሆነበት ገልጸው፣ በዚህም ከተማዋ እስከ ግማሽ ቢሊየን ብር ግብር እንደምታጣ አቶ አታክልቲ ተናግረዋል፡፡

ህገወጥ እርድ በተለይ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የጤና ችግር፣ አካባቢን የመበከልና ሌሎች ሰፊ ችግሮችን የሚያስከትል በመሆኑ ህብረተሰቡ እርድ በሚያከናውንበት ወቅት በህጋዊነት በቄራዎች ድርጅት በኩል እንዲያደርግም ገልጸዋል፡፡

የጭነት መኪናዎች በቀን በከተማዋ እንዳይንቀሳቀሱ ህግ የወጣ ቢሆንም፣ ድርጅቱ ግን አገልግሎቱ በበዓላት ቀናት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውይይት በማድረግ ፍቃድ ማግኘቱንም አቶ አታክልቲ አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይ 2012 ዓ.ም የሚያጋጥመውን የአገልግሎት ውስንነት ለመቅረፍ አዲስ ቄራ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም ተገልጿል፡፡

ግንባታው በ2012 ዓ.ም ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ በቀን እስከ 26 ሺህ እንስሳት የእርድ አገልግሎት የመስጠት አቅም ይኖራል ተብሏል፡፡