17 የምግብ ዘይት ምርቶች መሰረታዊ ችግር ስላለባቸው ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ባደረገው የገበያ ጥናት 17 የምግብ ዘይት ምርቶች ላይ መሰረታዊ ችግር በመስተዋሉ ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው አሳስቧል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው የገበያ ጥናት የዘይት ምርቶቹ የሚመረቱበት ቦታና የተመረተበት ሃገር ፣የምርት መለያ ቁጥር ፣የአምራች አድራሻ የሌላቸው፣የገላጭ ጽሁፍ ችግርና ለጤና ጠቀሜታ እንዳለው ተደርጎ የተቀመጠ፣የመጠቀሚያ ጊዜና ማብቂያ ቀን የሌላቸው እንዲሁም የሀገሪቱን የደረጃ ምልክት ያለጠፉና ደረጃውንም የማያሟሉ መሆናቸው በተደረገው ጥናት መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው የተባሉት የምግብ ዘይት ምርቶችም ሉሉ ዘይት፣ አርሲ ዘይት፣አሃዱ ዘይት፣ድሬ ንጹህ የምግብ ዘይ፣አሚን ንጹህ የምግብ ዘይት፣ሮያል የምግብ ዘይት፣ዳግም የተጣራ የኑግ ዘይት፣ጄጃን የምግብ ዘይት፣ውብ የተጣራ የኑግ ዘይት፣ለማ የኑግ ዘይት፣ኑድ ንጹህ የምግብ ዘይት፣ገበታ የምግብ ዘይት፣ዘመን ዘይት፣አጋር ዘይት፣አናጅና ዘይት ናቸው፡፡

በመሆኑ ህብረተሰቡ የትኛውንም የምግብ ምርት ከገበያ ሲገዛ የተመረተበትና የመጠቀሚያ የአገልግሎት ጊዜው ትክክለኛነት ፣ያልተፋቀና ያልተሰረዘ መሆኑን ፤የአምራች ድረጀቱ ስምና ሙሉ አድረሻ፣የምርት መለያ ቁጥር ያለው መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዛ የተጠየቀ ሲሆን ፤የምርት ገላጭ ጹሁፍ ይዘቶችን ያላሟላ ምርት ህብተሰቡ መግዛት እንደሌለበት ተገልጿል፡፡

ተመሳሳይ ምርቶች በሌሎች አካባቢ የመገበያያ ስፍራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉም ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ ፣ለፖሊስ አካላት ወይም በፌደራል ደረጃ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ ስልክ መስመር በ8482 በመጠቆም እንዲያሳውቅ ጠይቋል፡፡

በማያያዝም የክልል ተቆጣጣሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላት ምርቶቹን ከገበያ ላይ በአፋጣኝ የመሰብሰብ ስራውን እንዲሰሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡