3 የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ፈቃዶች ተሰጡ

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የማዕድናት ፍለጋ ለማካሄድ ፈቃድ ለጠየቀውና የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልቶ ለቀረበው አባይ ኢንደስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር 3 የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

ስምምነቱን በፈቃድ ሰጪው መስሪያ ቤት በኩል የፈረሙት ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሲሆኑ፤ በባለፈቃዶቹ በኩል ደግሞ የፈቃድ ወሳጅ ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡

ኩባንያው ፈቃድ ያገኘው በአማራ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ አካባቢዎች ሲሆን የከፍተኛ ደረጃ ሸክላ አፈር፣ የከፍተኛ ደረጃ ላይም ስቶን ማዕድን እንዲሁም የከፍተኛ ደረጃ የጅፕሰም ማዕድን ያመርታል፡፡

ኩባንያው ለኢንቨስትመንት ወጪ በአጠቃላይ 140,712,881.00 ( አንድ መቶ አርባ ሚሊዮን ሰባት መቶ አስራ ሁለት ሽህ ስምንት መቶ ሰማኒያ አንድ) ብር መድቧል ተብሏል፡፡ ባለፈቃዱ በምርት ወቅት በድምሩ ለ114 ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድልእንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፤ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና ማዳንም አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ለወጠነችው የኢንዱስትሪያዊነት መዋቅራዊ ሽግግር የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈልገውን የማዕድናት ግብዓት ለሟሟላት በሁሉም ዓይነት የዘርፉ ሃብቶቻችን ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡

የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን ፍላጎቱ ያላችሁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መዋዕለ ነዋያችሁን እያደገ በመጣው የማዕድኑ ዘርፍ ላይ እንድታውሉ እንጋብዛለን፡፡

የማዕድን ዘርፉ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩና ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው በሚሰራባቸው አካባቢዎች የአካባቢው ህብረተሰብ እና መንግስት አስፈላጊውን ትብርርና ድጋፍ ሁሉ እንዲያደረጉላቸው ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

የአካካቢ ጥበቃን በተመለከተ የሠራተኞቹን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳና ብክለት በማያስከትል መልኩ የምርት ስራውን ለማከናወን ኩባንያው ውል የፈፀመ ሲሆን ሥራውን ሲያቋርጥ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ፣ በሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም ዕፅዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውም ቅሪቶችና ግንባታዎችን ያስወግዳል። (ምንጭ፡-የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር)