ምክር ቤቱ የክልሉን የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብን ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ አፀደቀ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት ባካሄደው አምስተኛ የሥራ ዘመን አምስተኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉ የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብን ለማሻሻል በቀረበው አዋጅ ላይ በመምከር አፀደቀ።

ደንቡን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ኢንቨስትመንትን የክልሉን ልማት መደገፍ እና ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እንዲሁም ኢንቨስትመንት በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ እንደሆነ ተገልጿል።

ተሻሽሎ የሚቀርበው ደንብ በተለይ አርሶ አደሩ በኢንቨስትመንት ምክንያት ካሳ ተከፍሎት ከመሬቱ ላይ የሚሸኝበት ብቻ ሳይሆን በመሬቱ ላይ የሚካሄድ ኢንቨስትመንት ውስጥ ድርሻ ኖሮት ተጠቃሚ እንዲሆን ሁኔታዎችን የሚያመቻች ነው ተብሏል።

ግንባር ቀደም የሆኑ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ወደ ኢንቨስትመንት ልማት እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ላይ ያተኮረ መሆኑም ተነግሯል።

ደንቡ በክልሉ ውስጥ የሚካሄድ ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል በመፍጠር የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጡ ረገድ የራሱን ሚና እንዲኖረውም ያደርጋል።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት በነበረው የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሲታዩ የነበሩትን ጉድለቶች ከመሠረቱ በመቅረፍ ለኢንቨስትመንት የሚውሉ መሬቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ላይም ትኩረት ተሰጥቷል።

ጎታታ የነበረውን የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ሂደትን በመሻሻል እና ፈጣን የሆነ አገልግሎት በመስጠትም ኢንቨስትመንትን ወደ ክልሉ የመሳብ እና ኅብረተሰቡ በኢንቨስትመንት ውስጥ ያለው ተሳትፎን እንዲያሻሽል ለማድረግም ደንቡን ማሻሻል ማስፈለጉ ነው የተጠቆመው።

በዚሁ መሠረት የክልሉን የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ለማሻሻል የቀረበው አዋጅ፣ አዋጅ ቁ. 208/2012 ሆኖ እንዲፀድቅ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። (ምንጭ፦ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት)