ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላትና ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላትና ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡

ቢሮው ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ በከተማዋ የተለያዩ ህገወጥ አሰራሮችን በመጠቀም የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር ባደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ ፍተሻ ማድረጉን አስታውቋል።

 

የኮንትሮባንድ ንግድ ፣ ህጋዊ መስመርን ሳይከተሉና ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት መፈፀም ፣የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ፣ጥራት የሌላቸው ምርቶች ወደ ገበያው ማስገባት አና የህገ ወጥ ደላሎች መበራከት ለሸቀጦች ዋጋ መናር መንስኤ መሆናቸውን ነው የከተማዋ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊና የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ የተናገሩት።

ቢሮው ይህን ተከትሎ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ  ባደረጉ አካላትና ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በ5 ሺህ 700 የንግድ ተቋማት ላይ ፍተሻ ተካሂዶ ከእነዚህ ውስጥ 609ኙ ሲታሸጉ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑትም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 91 ወፍጮ ቤቶች፣ 93 ዳቦ ቤቶች፣ 56 አትክልት ቤቶችና 63 ስጋ ቤቶች ይገኙበታል፡፡

በቀጣይም ህጋዊ መስመር ተከትሎ የሚሰራውን ነጋዴ ማበረታታት እና ህጉን ጠብቆ እንዲሰራ ማድረግ ላይ በትኩረት ይሰራል ብሏል፡፡

የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተቱን ለመሙላትም ቢሮው ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም ነው የተገለፀው፡፡

ለአብነትም የአቅርቦት ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ 30 ሺህ ኩንታል የጤፍ ምርትን ለማዳረስ እየተሰራ እንደሚገኝ ተነስቷል፡፡

ቀደም ሲል በሀገሪቱ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮሚቴ ስራውን በባለቤትነት እየሰራ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በቀጣይም ህጋዊ እርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡