የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ በጥቅምት መጀመሪያ የሙከራ ኃይል ያመነጫል

254 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያስችለው ውሃ በግድቡ በመሙላቱ በጥቅምት መጀመሪያ የሙከራ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በገናሌ እና ዳዋ ተፋሰሶች በጉጂ እና ባሌ ዞኖች መካከል እየተገነባ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው።

በአሁኑ ወቅት በግድቡ ለተተከሉት ሶስት ተርባይኖች ማንቀሳቀሻ የሚሆነው እና ከግድቡ የታችኛው ወለል አንስቶ 70 ሜትር ከፍታ የሚደርሰው ውሃ በመሙላቱ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የሙከራ ኃይል ማመንጨት ይጀመራል።

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፤ በግድቡ እንዲገባ የተደረገው ውሃ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንኛዎች ታሪክ ረጅሙ በሆነው እና 12 ነጥብ 4 ኪሎሜትር በሚረዝመው የኮንክሪት ዋሻ ውስጥ አልፎ ነው ተርባይኖቹን የሚያንቀሳቅሰው።

በአሁኑ ወቅትም ዋሻው በውሃ ተሞክቶ የፍተሻ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። እስከአሁን ድረስ ያለውሃ እና በእርጥበት አማካኝነት በተደረጉ የተርባይን ፍተሻዎች የተሳካ ውጤት ተገኝቷል።

ሶስቱ ተርባይኖችም በሙሉ አቅም ሲሰሩ እያንዳንዳቸው 84 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላሉ፡፡

ግድቡ ጥቅምት ላይ የሙከራ ኃይል ማመንጨት ሲጀመርም የሚመረተው ኤሌክትሪክ በይርጋለምና ወላይታ ሶዶ ከተሞች አድርጎ አዲስ አበባ የሚገኘው ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እንዲገባና ወደሚያስፈልጉ አካባቢዎች እንዲሰራጭ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ 630 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ግንባታው የተጀመረው መጋቢት 2003 ዓ.ም ላይ ነው።

ከየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለግድቡ የሚሆን ውሃ ሙሌት ሲካሄድ ቆይቷል። ቀሪ ስራዎች የሚቀሩት ግድቡ 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያለው ሲሆን፤ ግንባታው በቻይናው ሲጂጂሲ ድርጅት እየተከናወነ ይገኛል።

ለግድቡ ወጪ የኢትዮጵያ መንግስት 40 ከመቶ ሲሸፍን የቻይናው ኤግዚም ባንክ ደግሞ 60 በመቶ የሚሆነውን ፋይንናንስ አቅርቧል።