ኢትዮጵያና እስራኤል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የስራ ዕድል መፍጠር በሚቻልባቸዉ መስኮች ዙሪያ ምክክር እያደረጉ ነዉ

ኢትዮጵያ ከእስራኤል የካበተ የቴክኖሎጂ አቅምና ልምድ አስፈላጊዉን ክህሎት በመቅሰም የበለጠ የስራ ዕድል መፍጠር በምትችልበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡

በጉባዉ ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጀማል በከር ኢትዮጵያ ከእስራኤል ሰፊ የቴክኖሎጂ ተሞክሮ ብዙ መማርና መጠቀም እንደምትችል አመልክተዋል፡፡

ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 73 በመቶ የሚሆነዉ ወጣት መሆኑንና ይህን ሃይል በመጠቀምና በቴክኖሌጂ የታገዘ የስራ ዕድል በመፍጠር አገሪቱን ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም ተወስቷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ በበኩላቸዉ እስራኤል በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ልምድ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየዉ የምክክር መድረክ በዘርፉ በኢትዮጵያ ያሉ ተግዳሮቶች፣ ምቹ ሁኔታዎች እንዲሁም የእስራኤል ልምድ ከዘርፉ ባለሙያዎች ምክክር እንደሚደረግበት ታዉቋል፡፡