የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 68 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱ ተገለፀ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 68 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።

በግራ ሃይል ማመንጫ ቤት የሚገኙት ሁለት የሃይል ማመንጫ ዩኒቶች ማለትም ዩኒት ዘጠኝ እና 10 የብረታ ብረት ገጠማ ስራ 50 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጂነር አብርሃም በላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ፡፡

ሁለቱ ተርባይኖችም በቅርብ ማመንጨት እንዲችሉ ሆኖ ስራቸው በፍጥነት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ እየተሰራ ያለው የሲቪል ስራ በመገባደድ ላይ ያለ መሆኑና በተቋራጩ እየተገነባ ያለው አጠቃላይ የሲቪል ስራ በፍጥነት እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካይ 15 ሺህ 670 ጊጋ ዋት በሰዓት ሀይል እንደሚያመነጭ ተናግረዋል።

ከግድቡ በታች ለሚለቀቀው ውሃ የሚያገለግለው ከዋናው ግድብ በስተግራ በኩል መዝጊያ ያለው የጎርፍ ማስተንፈሻ (ጌትድ ስፒልዌይ) ደግሞ 96 በመቶ ተጠናቋል ተብሏል።

ግድቡ የታቀደለትን ውሃ መያዝ እንዲችል እና የውሃውን ፍሰት ወደ ዋናው ግድብ እንዲሆን የሚያደርገው የግድቡ ክፍል የኮርቻ ቅርጽ ያለውና የኮቻ ግድብ በሚል የሚጠሩት (ሳድል ዳም) 96 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ዶ/ር ኢንጂነር አብርሃም፤ የኮርቻ ግድቡ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የ ሚጠናቀቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰሞኑን ከግብጽ ጋር ተያይዞ የተነሳው አለግባባት የውሃ አሞላል ላይ ግድቡን በረዥምጊዜ እንዲሞላ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው ኢንቨስትመንት ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑና የኢትዮጵያን ህልውና የሚጋፋ በመሆኑ ብቻ ኢትዮጵያ የግብጽን ምክረ ሃሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ ያደረገችው መሆኑን ተናግረዋል።

የግብጽ የተለየ አቋም በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ምንም ዓይነት ተጽእኖ እንደማያስከትል ዶ/ር ኢንጂነር አብርሃም ተናግረዋል።