የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በከፊል ስራ መጀመሩ ተገለፀ

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ 11 ሼዶች የተጠናቀቁ ሲሆን ከነዚህ መካከል 4ቱ ስራ ጀምረዋል፡፡

ፓርኩ 152 ሼዶች ይገነቡበታል ተብሎ የታቀደ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 11 ሼዶች ተጠናቀው 4ቱ ነው ወደ ስራ የገቡት ተብሏል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክን በጎበኙት ጊዜ  እንደተናገሩት ፓርኩ ለሀገር ኢኮኖሚ ካለው ፋይዳ በዘለለ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት፣ ዕድገትና ተጠቃሚነት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ወደ ስራ የገባው የአቡካዶ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ አንድ ማሳያ መሆኑንም ነው ምክትል ርዕሰ መስዳደድሩ የገለፁት፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ የአርሶ አደሩን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ርስቱ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የፓርኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብሩ ወልዴ በበኩላቸው ፓርኩ የምግብ ማቀነባበሪያ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የቀሪ ሼዶች ግንባታ የፋብሪካዎቹ አይነት ወይም ፍላጎት ሲታወቅ የሚገነባ ሲሆን፣ ተቋሙ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንዳለበት ሥራ አስፈፃሚው አክለው ጠቁመዋል፡፡