በህገ-ወጥ ደላሎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

በህገወጥ ደላሎች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ተናገሩ ፡፡

በሀገራችን በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በአገልግሎትና በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት በአቅርቦት ችግር ሳይሆን የህገወጥ ደላሎች ጣላቃ ግብነት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የዋጋ ንረቱ በተለይም በደሃው ማህበረሰብ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደሩም ባሻገር ጥቂቶች አላስፈላጊ ንዋይ በመሰብሰብ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲፈጠር አድርጓልም ብለዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በህገ- ወጥ ደላሎች አማካኝነት አየር በአየር በመኪና ላይ ህገወጥ ግብይት ሲያካሂዱ የተገኙ 59 መኪኖች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም 52 መኪኖች ጤፍና ሌሎች እህሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተናገሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ፤ ይህም የቁጥጥርና እርምጃ የመውሰድ ስራ በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ እንዳሚያመለክተው ደላሎችን ከሰንሰለት ውጪ በማድረግና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቾችና ተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚገናኙበትን አግባብ ለመፍጠር ሚኒስቴር መ/ቤቱ የረጅም ጊዜ እቅድ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡