በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ላይ ከክልል የካቢኔ አባላት ጋር ዉይይት ተደረገ

የገንዘብ ሚኒስቴር በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ላይ ከ9ኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከተዉጣጡ የካቢኔ አባላት ጋር ዉይይት አደረገ፡፡

ዉይይቱ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ላይ ያተኮረ ሲሆን አላማዉም ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ያስመዘገበችዉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አሁን ላይ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በመለየት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማምጣትና የኢኮኖሚ እድገትን ማስቀጠል ነዉ፡፡

በዉይይቱ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል አመራሩ በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቁበትና የተረጋጋ ማክሮኢኮኖሚ ለመፍጠር ከግብርናና ኢንዱስትሪ በተጨማሪ ሌሎች ዘርፎችም ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

አገሪቱ ያላትን የሰዉና ተፈጥሮ ሃብት በጥናት ላይ ተመርኩዞ በጥቅም ላይ ማዋልና በኢኮኖሚዉ ላይም የጎላ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸዉ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸዉ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ገለፃ ኢኮኖሚዉ ከገጠሙት ተግዳሮቶች መካከል ምርታማነትን ማሳደግ አለመቻል፣ የወጭና ገቢ ንግድ አለመመጣጠንና አገር በቀል ሃብቶች ላይ ትኩረት አድርጎ አለመስራትን በዋናነት አንስተዋል፡፡

በቀጣይም በተለይ በቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን፣ በግብርናና ሌሎች በኢኮኖሚዉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል በተባሉ ሴክተሮች ላይ በሪፎርሙ ትኩረት አድርጎ አለመስራትን በዋናነት አንስተዋል፡፡   

በሪፎርሙ በቀጣይ 10 አመታት የነፍስወከፍ ገቢን በ3 ዕጥፍ ማሳደግና ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም በዉይይት መድረኩ ተወስቷል፡፡