የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልሎች የድጎማ በጀት የማከፋፈያ ቀመርን ለሁለት ዓመት አራዘመ

የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚያደረገው የድጎማ በጀት የማከፋፈያ ቀመርን ለሁለት ዓመት አራዝሟል።

በስብሰባውም የ5ኛው የፓርላማ ዘመን 4ኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤውን አጽድቋል፡፡

ቀደም ሲል የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ደልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በ2010 በጀት ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የተጠበቀው የህዝብና ቤት ቆጠራ በወቅቱ ስላልተካሄደ አሁን ያለውን የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ለሶስት ዓመታት ብቻ እንዲያገለግል ተደርጎ ነበር፡፡

አሁን ላይ ግን በተለየዩ ምክንያቶች ቀመሩ ተግባር ላይ የሚውልበት ጊዜ እስከ 2014 በጀት ዓመት እንዲራዘም የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ የሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ደልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር በአንድ ዓመት ፤ ይራዘም የሚለው በ28 ድምጽ በሁለት ዓመት ይራዘም የሚለው ደግሞ በ48 ድምፅ በማግኘት እስከ 2014 ድረስ እንዲራዘም ተወስኗል፡፡

የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ስድስት ጉዳዮች እና የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ያላቸው ሁለት ጉዳዮችን በተመለከተ አባላቱ ተወያይተው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡