የአንበጣ ወረርሽኝን ለመከላከል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ

የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት የአንበጣ መረጃ ክፍል፣ አንበጣ መቼ ሊከሰት እንደሚችል ሀገራትን ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያም ከ2011 ግንቦት ጀምሮ ሊገባ እንደሚችል በነበረው ትንበያ መሠረት የነፋስን አቅጣጫ ተከትሎ ከሳውዲ አረቢያ ቀይ ባሕርን አቋርጦ በየመን በኩል ሰኔ መጨረሻ በአፋር ክልል ተላላክ ወረዳ ተከስቷል።

የግብርና ሚኒስቴር እንዳለው ይህ የአንበጣ መንጋ ከድንጋይ በስተቀር ሁሉንም ሰብሎች እና የዕፅዋት ዓይነቶች በሙሉ የሚበላ፣ የሀገራት ድንበር የማይገታው ድንበር ዘለል (ተዛማች) የአንበጣ መንጋ በቀን ከ150 እስከ 300 ኪ.ሜ የሚጓዝ፣ እጅግ አደገኛ ነፍሳት ስለሆነ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ሊፈታተን ይችላል።

እስካሁን በሰብል ላይ ያደረሰው ጉዳት ባይኖርም፣ በእንስሳት ግጦሽ፣ ደን እና ቁጥቋጦ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። ይህም ለእንስሳት ድርቅ በማምጣት፣ ምርት እና ምርታማነት በመቀነስ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጠባሳ ሊፈጥር ይችላል።

ግብርና ሚኒስቴር አንበጣ ወደ ሀገራችን እንደሚገባ መረጃው ስለነበረው በተከሰተበት ወቅት በአውሮፕላን ለማጥፋት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ኅብረተሰቡ ፀረ ተባይ ላይ ስጋት ስለነበረው ፈቃደኛ ባለመሆኑ አወያይቶ ለማሳመን ጊዜ በመውሰዱ አንበጣው ሊራባ ችሏል።

በብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ መረጃ መሠረት ዓመቱን ሙሉ በአብዛኛው አካባቢ ምቹ የዝናብ ስርጭት ስለሚኖር ይህ ደግሞ ለአንበጣ መራቢያ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በመሆኑም ይህ የአንበጣ ወረርሽኝ ወደ ሌሎች ክልሎች ተዛምቶ በሰብሎች እና ሌሎች ዕፅዋት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ የሚያስችሉ የማጥፋት ሥራዎች ላይ አርብቶ እና አርሶ አደሩ፣መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የልማት አጋር አካላት፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተዋናይ እንዲሆን የግብርና ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።