የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ሶስት ወራት ከእቅዱ በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ሶስት ወራት 56 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ  57 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የገቢ አፈፃፀምና ህገወጥ ድርጅቶች ላይ የተሰራውን ኦፕሬሽን ግኝትን አስመልከቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በሩብ ዓመቱ ገቢ ከታቀደው በላይ መሰብሰብ መቻሉን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡

በዚሁም ከሀገር ውስጥ ገቢ 31 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 24 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እና ከሎቴሪ ሽያጭ 46 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ እንደተቻል የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል ያሳዩት ተነሳሽነት እንደትልቅ ለውጥ የታየ ነው ብለዋል፡፡

166 ድርጅቶች በህገ ወጥ ድርጊት ተሰማርተው መያዛቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች፤ ከነዚህ 16ቱ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስራቸው ላይ ተግዳሮት የሆነውን የታክስ ስወራና ማጭበርበር የተሰማሩ ኃላፊነት የማይሰማቸው እንዳሉ ሁሉ በኃላፊነት በተገቢው መልኩ ግዴታቸውን የሚወጡትን የማበረታት ስራ እየተሰራ መሆኑንና ከነዚህም ውስጥ 163 የግብር ከፋዮች ተሸላሚ መሆን ችለዋል ብለዋል፡፡

የግብር ከፋዮችን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ከ19 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮችን ማስተማር እንደተቻለም ሚኒስትሯ ገልጸው፤በህገወጥ ስራ የተሰማሩ አካላት ለህግ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሳስበዋል፡፡