የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገለፁ

አዲስ አበባ ጥር 22/2004/ዋኢማ/– የኢፌዴሬ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የግብፅን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ከማል ኦምርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት ሁለቱ ሀገራት በማህበራዊ አገልግሎቶች በባለሙያዎችና ምሁራን ምክክሮች እንዲሁም በኢንቨስትመንት የፈፀሟቸው ስምምነቶች በታቀደው መሰረት ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛል።

ኢትዮጵያና ግብፅ በአካባቢው ጉዳዮች ላይ አቅማቸውን አቀናጅተው ለመስራት የጋራ አቋም መያዛቸውንም ነው አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል።

በሶማሊያ የአሸባሪው ቡድን አልሸባብ አቅሙ እየተዳከመ ባለበት ወቅት ግብፅና ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስቱን ለማጠናከር ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ከማል ኢምር በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

ግብፃዊያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢቨስትመንት እንዲሰማሩ መደረጉና በኢትዮጵያ ሁለት የኢንዱስትሪ ዞኖች መክፈታቸው የሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ በማለት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልፀዋል።

የኢትዮጵያና የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሀገራቱ ግንኙነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ የፖለቲካ የምክክር ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የሊቢያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሹር ቤን ካህያልን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በሊቢያ የጋዳፊ መንግስት ከስልጣን ከወረደ ወዲህ ኢትዮጵያና ሊቢያ ያደረጉት ይህ ውይይት የመጀመሪያው መሆኑን የኢሬቴድ ዘገባ ያመለክታል።