በአፋር ክልል ለቱሪስቶች ህልፈት ተጠያቂነቱን የመውሰድ ድርሻ የኤርትራ መንግስት ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 16 2004 /ዋኢማ / – በአፋር ክልል ለአምስት ቱሪስቶች ህልፈት ምክንያት ለሆነው የጃንዋሪ 16 /2012ቱ ጥቃት ከኤርትራ ውጪ ሃላፊነቱን ሊወስድ የሚገባው አካል እንደሌለ ማንም ሊጠራጠር አይገባም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ጥቃት አድራሾቹ በቀጥታ ከኤርትራ መጥተው በቱሪስቶች ላይ ጥቃቱን ከፈጸሙ በኃላ ወደ እዚያው ተመልሰዋል፡፡

ጥቃት አድራሾቹ ምን መስራት እንዳለባቸው በግልጽ አውቀው የተሰማሩ ሲሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን እያዘጋጀች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ግድያና እገታ መፈጸሙ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሻሻለ የመጣውን ገጽታዋን ማበላሸት የሚል አላማ ያነገበ መሆኑ ይታወቃል ብሏል፡፡

ኤርትራ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ጊዜ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ የቦንብ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገችው ያልተሳካ ሙከራ የሚታወስ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ሮይተርስ ትላንት በስም ያልተጠቀሰ ”አፋር ሪቮሊሽነሪ ዲሞክራቲክ ዩኒቲ ፍሮንት/አርዱፍ/” የተባለ የአማጺ ቡድን መሪን ዋቢ በማድረግ ቡድኑ በአፋር ክልል ለአምስቱ ቱሪስቶች ህልፈት ምክንያት ለሆነው ጥቃት ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ማለቱን ዘግቧል፡፡

አማጺ ቡድኑ ከኢትዮጵያውያን ወታደሮች ጋር ታግተው የተወሰዱ ጀርመናውያን ደህንነታቸው ተጠብቆ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጫ ሰጥተል፡፡” ሲልም ሮይተርስ ማተቱን ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ታጋቾቹን ”በአካባቢው በሚገኙ የአፋር የአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በሰላማዊ ድርድር እለቃለሁ ብሏል፡፡” ሲል ሮይተርስ መግለፁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በእርግጥ ይህ ስልት ኤርትራ ለቀጠለችበት ኢትዮጵያን የማተራመስ ድርጊት እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በኤርታሌ አካባቢ በአምስት ቱሪስቶች ላይ ለፈጸመችው ግድያ ሃላፊነት ላለመውሰድ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የተጠቀመችበት አዲስ የማወናበጃ ስልት ነው ሲል መግለጫው አስታውቋል፡፡

ኤርትራ ጸረ-ኢትዮጵያ ናቸው በሚል ራስዋ ለፈጠረቻቸው በርካታ ቡድኖች ድጋፍ እንደምታደርግ በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው ያለው መግለጫው እነዚህን ሃይሎችም ለቀጠለችበት ኢትዮጵያን የማተራመስ አላማዋ ማስፈጸሚያነት እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች ብሏል፡፡

በዚህ ሰዓትም በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው የማተራመስና አንገት የማስደፋት ተግባር ”አርዱፍ” በተባለው ቡድን ላይ መንጠልጠልን ዋነኛ ስልት አድርጋ መጠቀሟን አስታውቋል፡፡

በእርግጥ በሶማሊያና በአካባቢው የኤርትራን የማተራመስ ሚና እንዲመረምር የተሰየመው የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለቀጠለችባቸው መሰረተ ሰፊ የጥፋት ተልእኮ ተጠያቂ አድርጓታል ብሏል፡፡

አጣሪ ቡድኑ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ጁላይ 2011 ባወጣው ሪፖርቱ ገጽ 73 ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሁለት አመታት በፊት የጣለባትን 1907 የማእቀብ ውሳኔ በመተላለፍና ሃገር በቀል ተቃዋሚ ቡድን የሚል የውሸት ታርጋ የለጠፉ በራስዋ ትእዛዝና ቁጥጥር ስር ያደረገቻቸው የእጅ አዙር ሃይሎችን በመጠቀም በመላ አካባቢው አፍራሽ የትርምስ ድርጊቶችን በመፈጸም ተግባሯ እንደቀጠለችና ለዚህም ተጠያቂ እንደሆነች በግልጽ ማስቀመጡን ገልጧል፡፡

በቅርቡ ለፈጸመችው የቱሪስቶች ግድያም ተጠያቂ ከመሆን የምታመልጥበት ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም ያለው መግለጫው ግድያውን ፈጻሚዎቹ ግለሰቦች የመግደል፣ የመማረክና ጥቃታቸውን ፈጽመው ወዲያውኑ ወደ ኤርትራ ግዛት የመመለስ ተልእኮ አንግበው የመጡት በቀጥታ ከኤርትራ ከመሆኑ ላይ ምንም አይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም ብሏል፡፡

ኤርትራ በኢትዮጵያ በጉብኝት ላይ በነበሩ ቱሪስቶች ላይ በፈጸመችው ጥቃት መንግስት ቁጭት እንዳደረበትም መግለጫው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ለሟቾቹ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥለቅ ሃዘን በድጋሚ ይገልጻሉ ብሏል፡፡

ለተፈጸመው ግድያና እገታ ሁሉ ግን ተጠያቂነቱን የመውሰዱ ድርሻ የኤርትራ መንግስት መሆኑን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መግለጫ በመጥቀስ የዘገበው ኢዜአ ነው።