ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊነት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች

አዲስ አበባ ህዳር 19/2004/ ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዷን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ የሚያስፈልጋትን የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለመስጠት የሀገራቸው ፍላገት መሆኑን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሊመዩንግ ባክ ገለፁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በርዕሰ ከተማዋ ሴዑል ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ላይ እንዳሉት ደቡብ ኮሪያ በተለይም የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ የተጠናከረ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡

ሲ መዩንግ ባክ ባለፈው ሀምሌ ወር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት ካደረጉ ወዲህ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ጋር የትብብር መስኮች ላይ ሲመክሩ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የትብብር መስኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት የተያያዙ ስራዎች በፈጣን  ሁኔታ ላይ ወደ ተግባር እየተለወጡ መምጣታቸውን ገልፀው፤ ለዚህ ዋነኛ ማሳያው ደግሞ ኢትዮጵያ በደቡብ ኮሪያ የነበራትን ኤምባሲ ለሁለተኛ ጊዜ መክፈቷን አውስተዋል።

ውይይቱን ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በተዘጋጀው የራት ግብዣ ላይ  “የእናንተን ውለታ መቼም ቢሆን የምንረሳው አይደለም በማለት ይህ አመት በአጠቃላይ ከአፍሪካውያን ጋር ላለን ግንኙነት ክብር የምንሰጥበት ሆኖ እንዲታሰብ መወሰኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝቴ ያየሁት ነገር ሀገራችሁን ከድህነት ለማውጣት ከመቼውም በላይ ቁርጠኛ መሆናችሁን ነው በማለት የገለፁት ሲመዩንግ፤ ለዚህ ደግሞ የልማት ልምዶቻችንን በማካፈል አጋርነታችንን ማሳየት እንፈልጋለንም እናግዛችኋለንም በማለት ገልፀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጉብኝትን አስመልክቶ ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚለው፤ ደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ የአምስት ዓመቱን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ እንዲሳካ ድጋፍ ለማድረግ እቅድ አላት በተለይም በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ላይ የኮሪያን የልማት ልምድ በማካፈል።

ኢትዮጵያ ደቡብ ኮሪያን የልማት ሞዴል አድርጋ እንደምትወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደግሞ ወቅታዊ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከበፊቱ የተሻለ መልኩ እንደሚተባበር በሚያስችለን ሁኔታ ላይ ነን ብለዋል።

“እዚህ የመጣነው ድህነትን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ልንማር ነው። እዚህ የመጣነው ንግድና ኢንቨስትመንት እንዴት ማስፋፋት እንደሚቻል ልምድ ልንቀስም ነው። የደቡብ ኮሪያ የልማት ልምድ ለኛ ጠቃሚ ነው።” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተናግረዋል።

ለአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝ ወደ ደቡብ ኮሪያ ሴኡል የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ጋር በመሆን በኮርያ ብሔራዊ የሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጉብኝታቸውን በመቀጠል በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ  የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች ጋር በመገናኘት ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው የንግድ ልውውጥ ገለፃ የሚያደርጉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ የሚገኙ የኮርያ ባለሀብቶችም ልምዳቸውን ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢሬቴድ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።