የኢትዮጵያ፣ የግብጽና ሱዳን የጋራ የሚኒስትሮች ውይይት በውኃ ሃብት ልማት ታሪክ አዲስ የመተማመን መንፈስ የሚያጎለብት ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2004/ዋኢማ/– ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የጀመሩት የጋራ ሚኒስትሮች ውይይትና ትብብር በውኃ ሃብት ልማት ታሪክ አዲስ የመተማመን መንፈስ በማጎልበት በኩል ከፍተኛ አስታዋጽኦ እንደሚኖረው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የሦስቱ አገራት የሦስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ ሲካሄድ እንዳስታወቁት ውይይቱ በውኃ ሃብት ልማት መስክ አዲስ የመተማመን መንፈስን የሚያጎለብት ነው፡፡

የሚኒስትሮቹ የሦስትዮሽ ውይይት በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የጋራ ትብብር ለማድረግ አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዝ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በዓባይ ወንዝ ንኡስ ተፋሰስ የሦስቱን አገራት የጋራ ትብብርን ለማጎልበት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

እየተገነባ ባለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ያለባትን የኃይል እጥረት ከመቅረፉ ባሻገር ግብጽና ሱዳንን በኃይል አቅርቦት ረገድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የሦስቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ውይይት የአካባቢው አገራት የውኃ ሃብትን በተሻለ መልኩ ማልማት የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንላቸው አመልክተዋል፡፡

የግብጽ የውኃ ሃብትና የመስኖ ሚኒስትር ዶክተር ሄሻም ካንዲል በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በመገንባት ላይ በሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት የሚኖረው ተጽዕኖ ለመዳሰስ የሦስቱ አገሮች የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቅድሚያ ተነሳሽነት መውሰዷን አድንቀዋል፡፡

የሚቋቋመው ገለልተኛ የጋራ ኮሚቴም በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ግድቡ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ በመገምገም ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል፡፡

ይህም በሦስቱ አገራት መካከል ጥርጣሬን በማስወገድ የመተማመን መንፈስን እንደሚያጠናክር ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሦስቱ አገራት መካከል አዲስ የመግባባትና የትብብር ምዕራፍን የሚፈጥር መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የሱዳን የመስኖ እና የውኃ ሃብት ሚኒስትር ኢንጂነር ከማል ዓሊ በበኩላቸው ሦስቱ አገራት የሚያደርጉት ውይይት የተፋሰሱ አገሮች የሚያደርጉትን ትብብር እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱ የናይል ተፋሰስ አገሮች የተሻለ የትብብር መደረክ ለመፍጠር ጠንካራ መሰረት የሚጥል ይሆናል ብላ ሱዳን እንደምትጠብቅም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ግብጽ የጋራ ትብብራቸውን ለማጠናከር ከትናንት በስቲያ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸው የሚታወስ መሆኑን የኢዜአ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።