ሕገ-መንግስቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብዙህነታቸው፣ በአንድነታቸውና በውበታቸው ኮርተው እንዲኖሩ ያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2004/ዋኢማ/– ሕገ መንግሥቱ ብሔር ብሔሮችና ህዝቦች በብዙህነታቸው፣ በአንድነታቸውና በውበታቸው ኮርተው እንዲኖሩ ያስቻለ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃን አስታወቁ።

አፈ-ጉባዔው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ሕገ መንግስቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዙህነታቸው የስጋት ምንጭ ሳይሆን የአንድነትና የውበት መገለጫ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በየአመቱ እንዲከበር መደረጉ “ብዙህነታችን የስጋት ምንጭ ሳይሆን የአንድነታችን ምንጭ፣ የህብረታችን ምንጭና የውበታችን ምንጭ እየሆነ ሊሄድ እንደሚችል ምልክት እየሰጠ ያለ ነው” በማለት አፈ-ጉባዔው ካሳ ተክለብርሃን ተናግረዋል።

በመሆኑም የዘንድሮው ሕገ- መንግስቱ የፀደቀበትና የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል “ህገ-መንግስታችን ለብዙህነታችን፣ ብዙህነታችን ለአንድነታችን፣ አንድነታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል እንዲከበር የተደረገው በማለት ተናግረዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበር በተመለከተም ሲገልፁ፤ ከሌላው ጊዜ ለየት ባለ መልኩ የሚከበር መሆኑን ጠቁመው፤ በውጭ ያሉ ኤምባሲዎች አማካኝነት ኢትዮጵያውያን በዓሉን እንዲያከብሩት መደረጉንም ተናግረዋል።

እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ በሁሉም ትምህርት ቤቶች፣ መስሪያ ቤቶችና በሌሎች ተቋማት በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር፤ ሰፊ የሆነ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥር በዓል ይሆናል ብለዋል።

በዓሉ በሀገሪቱ መከበሩም በርካታ ጥቅሞች እንዳለው ገልፀው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር መሆኗን ለአለም ለማሳወቅ ከማስቻሉም በላይ የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ በማሳደግና ለመላው ዓለም ለማሳወቅ አስችሏቸዋል።

ይህም ዋንኛ ጠላታቸው የሆነውን ድህነትን በጋራ ተረባርበው እንዲያስወግዱ መንገድ እንደከፈተላቸው አፈ-ጉባዔው አቶ ካሳ ተክለብርሃን አመልክተዋል።

ሕገ-መንግስቱ በመፅደቁ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ያቀርቧቸው የነበሩ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ያስቻለ መሆኑንም ገልፀው፤ ምላሽ ያገኙትን ጥያቄዎችም ተግባራዊ ለማድረግ ብሔር ብሔረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መደራጀት ነበረባቸው ብለዋል።

በዚህ መሰረትም ባለፉት ዓመታት ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን አመራር በመምረጥና በማስተዳደር ማንነታቸውን በተግባር ማሳየት መቻላቸውን ገልፀዋል።

የሀገሪቱ እድገት የተመጣጠነ እንዲሆንና መላው ህብረተሰብ በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ሕገ-መንግስቱ የሚደነግግ መሆኑን የገለፁት አፈ-ጉባዔው የፌዴራል መንግስትም ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ ሁሉም ህዝቦች በእኩል እንዲጠቀሙ ቀመር እየሰራ እንደሚያከፋፍል ገልፀው፤  በቀጣዮቹ አመታትም ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በተለይ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ወሳኝና ቁልፍ ስራዎችን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣዮቹ አራት አመታት ስራ ላይ የሚውል አዲስ ቀመር እየሰራ መሆኑን አስታውቀው፤ ቀመሩን በህዝብ በማስተቸትና በማወያየት አፅድቆ ስራ ላይ እንደሚያውልም አመልክተዋል።

ሀገሪቱ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ለማሳካት ያቀደችው የአምስት አመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ውጤታማ ለማድረግ ቃል ኪዳን በመግባት በዓሉ  እንደሚከበርም ገልፀዋል።

በተለይም በህዳሴው ግድብ ላይ የታየው የህብረተሰቡ መነሳሳት ተአምር መስራት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን  የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ካሳ ተክለብርሃን መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።