በግብርናው ዘርፍ የልማት ሠራዊት በመገንባት ክልሎች ውጤታማ ስራ መስራታቸው ተገለፀ

አድስ አበባ፤ ታህሳስ 23 2004 /ዋኢማ/ – በግብርናው ዘርፍ የልማት ሠራዊት በመገንባት ረገድ ክልሎች ውጤታማ ስራ መስራታቸውን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው ገለፁ።

የግብርና ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሁለተኛው ዙር የፌደራልና የክልል አካላት የጋራ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ የልማት ሰራዊት ግንባታ እና የመስኖ ስራዎችን ማስፋት ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል ያሉት  ሚኒስትሩ የማስፋት እቅዱን ለመተግበር ወሳኝ የሆነውን የልማት ሠራዊት በመገንባት ረገድ ክልሎች ውጤታማ ስራ ሠርተዋል ብለዋል፡፡

በዘር ማባዛት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የተሰሩትን ስራዎች አበረታች  መሆናቸዉን የተናገሩት አቶ ተፈራ የመስኖ ልማትን በማስፋት ረገድም ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በመስኖ የለማው መሬት ስፋት ከአንድ አመት በፊት የነበረውን ሁለት እጥፍ ያህል ደርሷል፡፡ መስኖን በመጠቀም ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን በማምረት ረገድ የተከናወኑ ተግባራትም እመርታ ማሳየታቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ ይሁንና ሀገሪቱ ካላት በመስኖ ሊለማ ከሚችል መሬት ስፋት አንፃር ወደ ፊት የተጠናከረ ስራ ይጠብቀናል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ተፈራ ገለፃ የግብርና ቴክኖሎጂን ከማስፋት ጎን ለጎን አርሶ አደሩ አሟጦ የተጠቀመባቸውን ቴክኖሎጂዎችን ወደ ቀጣዩ የውጤት ምዕራፍ ሊያሸጋግር በሚችል መልኩ ማዳበር በምርምር ዘርፉ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሁለተኛው ዙር የፌደራልና የክልል አካላት የጋራ የምክክር መድረክ የፌደራል መንግስት ለክልሎች ድጋፍ ሊያደርግ የሚገባውን ጉዳዮች መለየት ተችሏል ያሉት አቶ ተፈራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውም የተጠናከረ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀዋል፡፡

መድረኩ የግብርናውን ዘርፍ ያለፉትን አምስት ወራት አፈፃፀም ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እንዲሁም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ያለመ ነው፡፡

በምክክር መድረኩ የአማራ፣ የትግራይና ደቡብ ክልሎች የግብርና ቢሮዎች ባለፉት አምስት ወራት ያከናወኗቸውን ስራዎች እና ተሞክሮዎች ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተሾመ ዋለልኝ ክልሉ የልማት ሰራዊት በመገንባት እና ሠራዊቱን ለማደራጀት የሚያስችል የአርሶ አደር ስልጠና በመስጠት ረገድ በስፋት መንቀሳቀሱን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የሰለጠኑት ከ47 ሺህ በላይ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወስደው በመተግበር እንደ ልማት ጣቢያ ሰራተኛ የሚያገለግሉ መሆናቸውን ዶክተር ተሾመ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው 2000 ያህል የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በቀበሌ ደረጃ ተመድበው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ እየተሳተፉ እንደሚገኙ እና ከጥር አንድ ጀምሮ በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና የተፋሰስ ልማት ስራዎች በስፋት እንደሚሰሩም ክልሉ ባቀረበዉ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል፡፡

የልማት ሰራዊት በመፍጠር 49 ሺህ 975 የልማት ቡድኖችን ማደራጀት የቻለው የትግራይ ክልልም በተመሳሳይ ለመስኖ ልማት አመቺ በሆነ የተፋሰስ ልማት እንደሚሰማራ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መዝገበ ፀጋዬ እንዳሉት በክልሉ 217 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ባለው ሂደት ከ50 በመቶ በላይ የሆነውን ማሳካት ተችሏል፡፡

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ በበኩሉ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ፣ የድርቅ ተጋላጭነትንና ተረጂነትን ለማስወገድ ትኩረት መስጠቱን አስታውቋል፡፡ የክልሉ የግብርና ቢሮ ተወካይ አቶ አበራ ሙላት ባቀረቡት ሪፖርት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የሌሎች ክልሎችን ልምድ በመቀመር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ በዚህ ዓመትም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተለይቶ የተፋሰስ ልማት ለመስራት ታቅዷል፡፡

በአስር ነጥብ ዘጠኝ  ሚሊዮን ብር ወጪ 1023 ኩንታል የቡና ዘር እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበራ ዘንድሮ አርሶ አደሩ በነፍስ ወከፍ ቢያንስ 250 የቡና ችግኞችን እንዲያለማና ሰፋፊ ቦታ ባላቸው አካባቢዎችም እስከ 1500 የቡና ችግኞችን የማልማት እቅድ መያዙን የዘገበዉ ኢሬቴድ ነዉ፡፡