ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተሰነቀው ራዕይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ሊደገፍ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2004/ዋኢማ/- ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ የሰነቀችው ራዕይ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ውጭ እውን ሊሆን እንደማይችል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ገለጹ።
 
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ማህሙዳ አህመድ ገአስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጉባዔን ትናንት በከፈቱበት ወቅት እንዳስታወቁት አገሪቷ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ የሰነቀችው ራዕይ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ውጭ ሊሆን አይችልም።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአንድ አገር የዕድገትና የህልውና መሠረት እንደመሆኑ መጠን ለዘርፉ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መንግሥት የመስኩን ወሳኝ ሚና በመገንዘብ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ ትምህርት እንዲስፋፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የከፍተኛ ምሁራን የተቀናጀ እንቅስቃሴ ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃን ለመለወጥ ጠንካራ የመስኩ አካዳሚዎች በስፋት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

አካዳሚው ከተመሰረተ በጣም አጭር ዕድሜ ቢኖረውም፤ አገሪቷ የሰነቀችው ራዕይ በማሳካት በኩል የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደምሴ ሃብቴ በበኩላቸው ጉባዔው “ሳይንስና ቴክኖሎጂ-የአገር ህልውና መሠረት” በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ለጉባዔው የተመረጠው መሪ ቃልም አካዳሚው የአገሪቷን የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ አቅምን በማጠናከር ለልማት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ጉባዔው በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉትን ለውጦችና አገሪቱ የምትገኝበትን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሁኔታን በመገምገም ከዘርፉ የሚገኘው ዕውቀት ምርታማና አዋጪ ለሆኑ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ቀረጻ ማዋል በሚቻልበት ዙሪያ በጥልቀት እንደሚመክር አስረድተዋል።

አካዳሚው ከተፈጠሮ ሳይንስ፣ ከግብርና፣ ከቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ፣ ከማህበራዊ ሳይንስና ሂዩማኒቲስ በተወጣጡ 49 ምሁራን መመስረቱንም ተናግረዋል።

በአሜሪካ የፐርድዩ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ በዚሁ ወቅት እንገለጹት በዓለም ላይ ያለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ አገር የለም።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰጡት ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በጉባዔውም “የአፍሪካ ግብርና-እያደገ በመጣው የዓለም ተግዳሮት ፊት” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

አካዳሚው የኢትዮጵያን የሳይንስ ባህልን ለማሳደግ ማዕከል አድርጎ እንደሚሰራ ለማወቅ ተችሏል።

በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች የወጣቶች የሳይንስ ማዕከላትን በማቋቋም የመጪው ጊዜ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መሪ ለማድረግ አካዳሚው እንደሚሰራ የኢዜአ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጠቁሟል።