ለሱዳን ሰላም ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ 7 ቀን 2004 (ዋኢማ) – በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሁሴን አልበሽር የተላከ ልዩ መልዕክት ዛሬ ምሽት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል በሰላም፣ በድንበርና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ለመፍታት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች።
 
በተለይ ሁለቱን አገራት በንግድና በኢንቨስትመንት ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ገልጸዋል።

ጄኔራል አብዱራሂም መሐመድ ሁሴን ከፕሬዚዳንት ኦማር ሁሴን አልበሽር የተላከውን ልዩ መልዕክት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ጉዳይ ትኩረት ሰጥታ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት።
 
ሁለቱን አገራት በሰላም፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማስተሳሰር ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ጉዳይ በመፍታት ረገድ ውጤት እየታየበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነም ጄኔራል አብዱራሂም ጠቁመዋል።

የሁለቱ አገራት የድንበር ማካለል ሥራም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

(ENA)