15 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለመስኖ ልማት ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2004/ዋኢማ/ – በመላው ሀገሪቱ 15ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለመስኖ ልማት ዝግጁ መደረጉን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ለመስኖ ዝግጁ የተደረገው 14 ሺ 998 ሄክታር መሬት በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤትነት የሚሰራ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ነው።

በሀገሪቱ 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ የገለፁት አቶ ብዙነህ፤ እስከ አሁን ድረስ 159 ሺ 276 ሄክታር መሬት በመካከለኛና ከፍተኛ መስኖ እየለማ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ሀገሪቱ ካላት ስፋት ያለው በመስኖ ሊለማ ከሚችለው መሬት ጋር ሲነፃፀር ሽፋኑ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ ላይ የመስኖ ልማት ሽፋኑን 15 በመቶ ለማድረስ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

እቅዱን ለማሳካትም በ14 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር 10 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ በዘንድሮ የበጀት ዓመትም 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ ወጪ ተደርጎ የልማት ስራው በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ነው።

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ማልማት ሲጀምሩ 153 ሺ 810 አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ሁለት የስኳር ፋብሪካዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።