ደቡብ ኮሪያ በትራንስፖርትና በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ዘርፍ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት

አዲስ አበባ፤ ጥር 04 2004 /ዋኢማ/ – የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ሥርዓት ለማሻሻልና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ለማጠናከር ደቡብ ኮሪያ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ሥርዓት ለማሻሻልና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ለማጠናከር የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ ጋር በትብብር ያዘጋጀው ጥናት ይፋ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ጆንግ ጌዩን ኪም በአውደ ጥናቱ ላይ እንደተናገሩት ደቡብ ኮሪያ በትራንስፖርትና በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ዘርፎች ያላትን የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት።

ባለፈው ዓመት የሁለቱ አገራት መሪዎች ባደረጉት ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ የነደፈችውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንድታሳካ ደቡብ ኮሪያ ያላትን ሰፊ ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረጉት ጉብኝት አረጋግጣለች ብለዋል።

የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ በበኩላቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ዘርፍ ደቡብ ኮሪያ ያላትን የዳበረ ልምድ በመጠቀም በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኢንተርፕራይዝ ሥራ እንደሚይዙ ተናግረዋል።

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ደቡብ ኮሪያ ያላትን ተሞክሮ እንደ ግብዓት በመጠቀም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እንዲስፋፋ ይደረጋልም ብለዋል።

በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከመካከለኛና ከትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ ያላትን ምርጥ ልምድ በመጠቀም የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ሥርዓትን ዘመናዊ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ውጤታማ የሆኑ የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኢንተርፕራይዞች በደቡብ ኮሪያ ያለውን ልምድ ሄደው እንዲጎበኙ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ አለማየሁ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የጀመረችው የልምድ ልውውጥና የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የደቡብ ኮሪያ ኤክስፐርት ኮንሰልቲንግ ግሩፕ ዳይሬክተር ዶክተር ክዩንግ ሱን ሶንግ ባደረጉት ንግግር ደቡብ ኮሪያ በኢንዱስትሪና በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ታካፍላለች ብለዋል።
እንዲሁም አገሪቱ በኢኮኖሚ ዕድገት አሁን ለደረሰችበት ደረጃ በማህበራዊ፣ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎችም ዘርፎች ያላትን የዳበረ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ በማካፈል ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያሳዩ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የገለጹት ዶክተር ሶንግ አገሪቱ አሁንም የምታስመዘግበው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን በምትጓዝበት ፍጥነት ከተራመደች ደቡብ ኮሪያ የደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ አጭር ጊዜ እንደሚወስድባትም ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።