ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 07 2004 /ዋኢማ/ – ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ በሚቀጥሉት አራት አመታት የሚገኘውን አመታዊ ገቢ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ስርጀቦ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የቆዳውን ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም ለመገንባትና በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ቁጥር በመጨመር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

ዘርፉን ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ የቤንችማርኪንግ፣ የነባር ገበያዎችንና አዳዲስ ገበያዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን የመለየት፣ የማስፋፋትና የቁርኝት መርሀ-ግብር የማውጣት ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን አጠቃላይ ገቢ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በማቃለል በኩልም ያለው ፋይዳ ቀላል የማይባል ነው ብለዋል።

ስትራቴጂው በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን በብዛት በመፍጠርና  ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በማቀናጀት ልምዳቸውን እንዲያጎለብቱ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋልም ብለዋል።

እንዲሁም የቆዳው ኢንዱስትሪ ዘመናዊ የስራ አመራር ዘዴዎችና አስተሳሰቦችን እንዲያስፋፉ በማድረግ የበለጠ ውጤት እንዲመዘገብ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

ከቆዳው ኢንዱስትሪ ባለፉት ስድስት ወራትም ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት ከተላኩ ምርቶች 80 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቁመው፤ ይህም የእቅዱን 86 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል።

እቅዱን መቶ በመቶ ማድረስ ያልተቻለው በዘርፉ የጥሬ ቆዳ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ስላጋጠመ መሁኑንም አስረድተዋል።