«አዲስ የወጣው የሊዝ አዋጅ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ህብረተሰብና ልማታዊ ባለሀብቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው »ጠ/ሚ መለስ

አዲስ አባባ፤ የካቲት 1/2004 (ዋኢማ) – ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፉት ስድስት ወራት መንግስት በፖለቲካ ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የነበረውን አፈፃፀም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒትሩ እንዳሉት በ2003ዓ.ም የነበረው እድገት ከትንበያ አልፎ እርግጠኛው አሀዝ ታውቋል፡፡ 11ነጥብ 4 በመቶ ፡፡

በዚህም ግብርና 9 በመቶ ኢንዲስትሪ 15 በመቶ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ 12 ነጥብ 5 በመቶ አድጓል፡፡

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች የዋጋ ግሽበቱ ከነበረበት 40 ነጥብ 6 በመቶ በጥር ወር ወደ 32 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሂደቱ በዚህ ከቀጠለ የዋጋ ንረቱ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ አንድ አሀዝ ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ግብር ለመሰብሰብ በተደረገ ጥረት ባለፉት ስድስት ወራት ከ35 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገቢ መገኘቱን አቶ መለስ ገልፀዋል፡፡ ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 41 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የወጣው የሊዝ አዋጅ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍልና ልማታዊ ባለሀብቱን የሚጠቅም እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡

በከተሞች አካባቢ የመንግስት መዋቅርን ሳይቀር እያበላሹ ናቸው ባሏቸው ላይ ፤ የመሬት ንግድና ግብር ላይ መንግስት የጀመረውን የአሰራር ማሻሻያ እንደሚያጠናክር ነው ጠ/ ሚ መለስ የገለፁት።

ከሊዝ አዋጁ ጋር በተያያዘ ስለ ነባር ይዞታዎች የሚናፈሱ ወሬዎች ፈፅሞ የተሳሳቱና አዋጁ ውስጥ ያልተካተቱ እንደሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

መንግስት በቀጣይ የንግድ ስርዓቱ ለሰላማዊ ውድድር የሚመች እንዲሆን ለማድረግ የጀመራቸውን ተግባራት እንደሚገፋበትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተናገሩት።

በግብር አሰባሰብ ሂደት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የሀገሪቱን የግብር አሰባሰብ ሂደት ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተናግረዋል፡፡