አዋጁ የኢንዱስትሪ ሠላም በማስፈን ምርትና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 02 2004/ዋኢማ/ -አዲሱ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና አዋጅ የኢንዱስትሪ ሠላም በማስፈን ምርትና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ገለፁ።

አዋጁ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶችና አገሪቱ ያወጣቻቸውን ሕጎች ፣ፖሊሲዎችና የልማት ዕቅዶች ተፈፃሚ ለማድረግ እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው በላይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት የአዲሱ አዋጅ ስራ ላይ መዋል ለአገሪቱ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ትልቅ ፋይዳ አለው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ አዋጁ ሠራተኞች በሥራ ላይ ለሚያጋጥማቸው ማናቸውም አካላዊ ችግሮች ዋስትና ስለሚሰጥ የተረጋጋ ሕይወት በመምራት ምርታማነታቸውን ያሳድጋል፤ለኢንዱስትሪዎችም ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠርና የኢንዱስትሪ ሠላም በማስፈን ትርፋማ እንዲሆኑ ያግዛል።

ሠራተኞችም ሆኑ የአሰሪ ተቋማት ትርፋማ ሲሆኑ አገር ትጠቀማለች ያሉት አቶ ጌታቸው አዋጁ የዜጎችን ማህበራዊ ደህንነት በማረጋገጥ የተረጋጋ ሠላም በመፍጠር ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።

አዋጁ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ድንጋጌዎች መነሻ ማድረጉን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች፣የአለም የሥራ ድርጅት ያወጣቸው የማህበራዊ ዋስትና ማዕቀፎችና የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ለመተግበር የተደረጉ ስምምነቶች ዋነኞቹ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ያወጣቻቸው ሕጎች፣ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎችና የልማት ዕቅዶችም አዋጁን ሥራ ላይ ለማዋል በመነሻነት ተወስደዋል።

በአገሪቱ ሕገ መንግስት ለሁሉም ዜጎች የማህበራዊ ዋስትና መረጋገጥ እንዳለበት ተደንግጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሕዝቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለሙ በመሆናቸው ለአዋጁ መውጣት በመነሻነት ተወስደዋል።

በአምስት አመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማሳደግና በአገር ውስጥ ያሉ የማህበራዊ ዋስትና ፕሮግራሞችን ለማስፋት ትኩረት መሰጠቱንም በመነሻነት ጠቅሰዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ባለፉት ስድስት ወራት ኤጀንሲው አዋጁን ለማስፈፀም የተቋሙን አቅም በመገንባት፣የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል።አዋጁ አዲስ እንደመሆኑ በሠራተኞች ዘንድ የሚታየውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታት ኤጀንሲው በፌዴራልና በክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

እስካሁን በተለያዩ ክልሎች የተካሄደው ምዝገባና መዋጮ የማሰባሰብ ሥራ አመርቂ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የጡረታ ማህበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ ለመሆን መመዝገባቸውን ተናግረዋል።ኤጀንሲው በፌዴራል ደረጃ ብቻ የነበረውን መዋቅር ወደ ክልሎች በማስፋት በኦሮሚያ፣ደቡብ፣በአማራና በትግራይ ክልሎች ፅሕፈት ቤቶችን ከፍቷል፤በተቀሩት ክልሎችም ፅሕፈት ቤቶችን ለመክፈት በቅጥር ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን እና በሠራተኞች ሲነሳ የነበረና የተለያዩ ጥናቶች ሲካሄዱ እንደነበረ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ከአምስት አመት በፊት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት መደረጉንና በተለይ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ የአዋጁን አላማና መነሻ ያለመረዳት ችግር እንደነበር ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው እስካሁን ካጋጠሙት ችግሮች የግንዛቤ ችግር አንዱ መሆኑን ያወሱት አቶ ጌታቸው የህብረተሰቡ የቁጠባ ባሕል አናሳነትም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።እነዚህንና ሌሎች በፕሮቪደንት ፈንድና በጡረታ ማህበራዊ ዋስትና መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማሳወቅ ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና አዋጅ ከሐምሌ 2003 ዓ/ም ጀምሮ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወቃል።