ኢትዮጵያ ለከፍተኛ ትምህርት የምታደርገው የሙአለ ነዋይ ፍሰት እያደገ መምጣቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2004/ ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምታደርገው የሙአለ ነዋይ ፍሰት እያደገ መምጣቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም “ከፍተኛ ትምህርት ለልማት” በሚል መሪ ሐሳብ አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት አጋርነት ጉባዔ ትናንት በከፈቱበት ወቅት እንዳስታወቁት አገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋትና ለውጥ ለማምጣት የምታፈሰው ሙአለ ነዋይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከሁለት ያልበለጠ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ አሁን ግን መንግሥት በሚያፈሰው ከፍተኛ ሙአለ ነዋይ ቁጥራቸው ወደ 32 ማደጉን አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ለትምህርት ከሚመድበው ጠቅላላ በጀትም 18 በመቶ የሚሆነው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስፋፊያና የለውጥ መርሃ ግብር ማስፈጸሚያ እንዲውል መደረጉ ለዘርፉ የተሰጠውን የኢንቨስትመንት ትኩረት ያመላክታል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለተቋማቱ ማስፋፊያ ከፍተኛ ገንዘብ ሲያፈስ አገሪቷ የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ከተቋማቱ ዕድገት ውጭ እውን እንደማይሆን በመገንዘቡ ነው ብለዋል።

የአገሪቱን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልማት በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ለመገንባትም ከአሜሪካ መንግሥትና ዩኒቨርስቲዎች ጋር በአጋርነት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን የልማት መሠረት ነው ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ይህን የልማት ተልዕኮ ለማሳካት የዓለም አገራትና መሰል ተቋማት በአጋርነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ተወካይ ሚስስ ሜሪ ካትሪን ፊ በበኩላቸው፤ በአፍሪካና በአሜሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ይህም የአፍሪካ መንግሥታት የሰው ኃብት፣ ልማትና ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት የሚደግፍ ኃይል አስገኝቶላቸዋል ብለዋል፡፡

ያም ሆኖ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው የፆታ ስብጥር የተመጣጠነ አለመሆኑ ሴቶች በአፍሪካ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳይኖራቸው ማድረጉን ተወካይዋ ተናግረዋል፡፡

መንግሥታት በከፍተኛ ትምህርት ለሥርዓተ ጾታ እኩልነት መረጋገጥ ትኩረት እንዲሰጡ የጠየቁ ሲሆን፣ የአሜሪካ ሕዝብና መንግሥትም አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አድማሱ ጸጋዬ የጉባዔውን ዓላማ አስመልክተው እንደተናገሩት ጉባዔው የአፍሪካና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለልማት ተቀናጅተው ለመሥራት በጋራ የሚመክሩበት ነው፡፡

በጉባዔው በዓለም ባንክ ባለሙያዎችና በሌሎች ምሁራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል፡፡

ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ይኸው ጉባዔ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት/USAID/ በጋራ እንዳዘጋጁት የኢዜአ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።