በኔዘርላንድስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከ200 ሺህ ዩሮ በላይ አሰባሰቡ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7ቀን 2004 (ዋኢማ) – በኔዘርላንድስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ200 ሺህ ዩሮ በላይ (ከ4ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ያህል)ማሰባሰባቸውን በአገሪቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ገለጹ፡፡

በኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተወካይና የማስተባበሪያው ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዓለማየሁ ስንታየሁ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ እንደገለጹት በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመጀመሪያው ምዕራፍ ለግንባታው የሚውለውን ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡

በአገሪቱ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በግድቡ ግንባታ ላይ ታሪካዊ አሻራቸውን ለማሳረፍ ቦንድ በመግዛትና ድጋፍ በማድረግ ገንዘቡ መሰብሰቡን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በቅርቡም የአንደኛ ምዕራፍ የድጋፍና የቦንድ ግዢ ተጠናቆ ገንዘቡ ገቢ የሚደረግ ሲሆን፣ ቀጣዩን ምዕራፍ ለመጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡

በኔዘርላንድስ የሚኖሩ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች የግድቡን ግንባታ ጨምሮ የአገሪቱን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ለመደገፍ ከፍተኛ መነሳሳት እያሳዩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የዲያስፖራውን ከፍተኛ ንቅናቄ በተቀናጀ መልኩ እንዲፈጸም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የግድቡን አስተባባሪ ምክር ቤት አቋቁመው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

በኔዘርላንድስ ከ12 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተያያዘ ዜና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሕዳሴው ግድብና በአገሪቱ አጠቃላይ የልማት ሥራ የበኩላቸውን ለመወጣት ከፍተኛ ንቅናቄ መፍጠራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡

በሚኒስቴሩ የዲያስፖራ መረጃና ጥናት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወልዴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው አገሮች የተፈጠረውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በተደራጀ መልኩ ማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ምክር ቤቶች አቋቁመው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
|
የምክር ቤቶቹን የሥራ እንቅስቃሴ ለመደገፍም በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች አስፈላጊውን መረጃና እገዛ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በቅርቡ እንደሚጸድቅ የሚጠበቀው ረቂቅ የዲያስፖራ ፖሊሲ በ22 የውጭ አገሮች ከተሞች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ውይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙትን ገንቢ ግብዓቶች እንዲካተቱ በማድረግ ረቂቅ ፖሊሲው እንዲጸድቅ ለሚመለከተው አካል ይቀርባልም ብለዋል፡፡

በቅድሚያ ግን በአገር ውስጥ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ጋር በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በዚህ ወር ውይይት እንደሚደረግ አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል፡፡

ረቂቅ ፖሊሲው ሲጸድቅ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይና ልማት የሚኖራቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ያጎለብተዋል፡፡

መንግሥት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከዲያስፖራው እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ አስተዋጽኦ እንደሚጠብቅ ሚኒስቴረን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።