በሚቀጥሉት አራት አመታት ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ 500 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ የካቲት 11/2004 (ዋኢማ) – ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ በሚቀጥሉት አራት አመታት የሚገኘውን አመታዊ ገቢ ወደ 500 ሚሊየን ዶላር ለማድረስ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የቆዳውን ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም መገንባትና በዘርፉ ያለውን ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሀይል ቁጥር መጨመርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

እንዲሁም ዘርፍን ለማሳደግ የቤንችማርኪንግ፣ የነባር ገበያዎችንና አዳዲስ ገበያዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን የመለየት፣ የማስፋፋትና የቁርኝት መርሀ-ግብር የማውጣት ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን አጠቃላይ ገቢ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በማቃለል በኩልም ያለው ፋይዳ ቀላል የማይባል ነው ብለዋል።

ስትራቴጂው በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን በብዛት በመፍጠርና ጥረታቸውን ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በማቀናጀት ልምዳቸውን እንዲያጎለብቱ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋልም ብለዋል።

እንዲሁም የቆዳው ኢንዱስትሪ ዘመናዊ የስራ አመራር ዘዴዎችና አስተሳሰቦችን እንዲያስፋፉ በማድረግ የበለጠ ውጤት እንዲመዘገብ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በቆዳ አልባሳትና ምርት ውጤቶች ላይ ከ150 ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፍ ለማሰልጠን የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ሰልጣኞች በቦርሳ፣ ጫማ፣ ቀበቶ፣ የኪስ ቦርሳና በሌሎች የቆዳ አልባሳት ምርቶች ላይ አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

ስልጠናውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለመስጠት መታቀዱን  ጠቁመው፤ የስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የስራ ቦታ በማመቻቸት ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የገለፁት።

የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት እስማኤል ሁላላህ ወደ ተቋሙ በመምጣቱ እድለኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከተቋሙ በሚወጣበት ወቅትም በመደራጀት ለመስራት አቅዷል፡፡

“እየተሰጠ ያለው ስልጠና በጣም ጠቃሚ ነው። ቀደም ሲል ስለ ጫማ አሰራር ብዙም ግንዛቤ አልነበረንም። እዚህ ትምህርት ቤት ከገባን በኋላ ግን ጠለቅ ያለ እውቀት እያገኘን ነው። የትኛው ቆዳ ለየትኛው ጫማ ይውላል የሚለውን በቀላሉ ማወቅ  ችለናል በማለት ይናገራሉ።”