አዲስ አበባና ካርቱም በከተማ ልማት ዘርፍ ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አባባ፤ የካቲት 14/2004 (ዋኢማ) – በአዲስ አበባና በካርቱም ከተሞች መካከል በከተማ ልማት ዘርፍ ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሞቱማ መቃሳ ከካርቱም ከተማ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ኢንጅነር አልረሺድ ኡስማን ፈቂ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ እ.ኤ.አ በታህሳስ 2010 በሁለቱ ከተሞች ከፍተኛ ኃላፊዎች መካከል የተፈረመውን መግባቢያ ስምምነት ለማስፈፀም የሚያስችል ነው፡፡

አምስት አባላት ያሉት የካርቱም ቴክኒክ ኮሚቴ ልዑክ በሁለት ቀናት የአዲስ አበባ ቆይታው የአነስተኛና ጥቃቅን የስራ ዘርፍ እንቅስቃሴን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የቤቶችና መሠረተ ልማቶች እንቅስቃሴን ይጎበኛል፡፡

ተመሳሳይ የአዲስ አበባ ልዑክም በመጪው ግንቦት ካርቱም በመሔድ በባህል፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በከተማ ግብርና ዘርፍ ልምድ እንደሚቀስም የመግባቢያ ስምምነቱ ሰነድ ማመልከቱን ኢሬቴድ ዘግቧል፡፡