የናይል ተፋሰስ አገሮች ሕጋዊ የትብብር የስምምነት ማዕቀፍ ወሳኝ ምዕራፍ መድረሱን ሚኒስቴሩ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/ 2004 (ዋኢማ) – የናይል ተፋሰስ አገሮች ሕጋዊ የትብብር የስምምነት ማዕቀፍ ወሳኝ በሆነ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ የናይል ቀን “የናይል ትብብር ለውኃ፣ ለኃይልና ለምግብ አቅርቦት” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በሚኒስቴሩ የተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ብሔራዊ የናይል ቀን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ሲከበር በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ቀደም ሲል በስድስት የተፋሰሱ አገሮች የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ በአገሮቹ ፓርላማ አሊያም ርዕሳነ ብሔራት ጸድቆ ተግባራዊ ወደሚሆንበት ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ለአሥር ዓመታት ያህል በተፋሰስ አገሮቹ ውይይትና ድርድር ሲደረግበት የቆየው ይኸው የትብብር ሰነድ በየአገሮቹ ሲጸድቅ አስገዳጅ ሕግ ይሆንና ሰነዱን ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ተግባራዊ እንቅስቃሴው ሲጀመርም ቀዳሚው ሥራ የናይል ተፋሰስ ቋሚ ኮሚሽን ማቋቋም እንደሚሆን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ በተፋሰሱ ውስጥ የሚካሄደውን ልማት የማቀድ፣ አተገባበሩን የመርዳት፣ የውኃ አጠቃቀሙን የመምራትና ውኃው በዘላቂነት ተጠብቆ ልማት ላይ እንደሚውል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማካሄድ ስትወስን የትብብር መንፈሱን በማይነካ መልኩ እንደሆነ ገልጸው፣ የግድቡ ዲዛይን የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ተጠቃሚነትን ታሳቢ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ጎርፍ፣ ትነትና ደለልን በመከላከል ረገድ ግድቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ ከግድቡ በሚመነጨው ኃይል አገሮቹን በኃይል አቀርቦት ማስተሳሰር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ሰነዱ የናይል ውኃን አጠቃቀም የሚወስን ሕጋዊ የትብብር የስምምነት ሲሆን ስምምነቱን ያልፈረሙ አገሮች ጠቃሚነቱን ተገንዝበው ይፈርሙታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበዳ ገርባ በበኩላቸው የናይል ውኃን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች መጠቀም እንዲችሉ የተጠናከረ ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ አማካይነት የሚሳለጠው የተፋሰሱ አገሮች ትብብርም ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ብሎም ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ያለው ፋይዳ ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢኒሼቲቩ የምስረታ ቀን ለማክበር በውኃና ኢነርጂ ልማት ያተኮረው መሪ ቃልም ኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረችው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር የተጣጣመ ሲሆን፣ በተፋሰሱ አገሮች መካከል የኃይል ሥርጭትና የንግድ መልካም ዕድልን ያስገኛል ብለዋል፡፡

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዌል ክሄሪይ በበኩላቸው በተፋሰሱ አገሮች መካከል ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተካሄዱ መሆናቸውን በተወካያቸው በኩል ገልጸዋል፡፡

በተለይ የተፋሰስ አገሮቹን በኃይል ንግድ፣ በግብርና፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በሌሎች ዘርፎች በማቆራኘት ለክፍለ አህጉራዊ ውህደት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የተፋሰሱ አገሮች በሚፈጠሩት የትብብር ማዕቀፍ ለተፋሰሱ ሕዝቦች የጋራ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት መረጋገጥ ፍትሃዊና ዘላቂ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ኢኒሼቲቩ ከተመሰረተበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1999 ጀምሮ ለተፋሰሱ አገራት ፕሮጄክቶች ማስፈጸሚያ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር እንዲያገኙ እገዛ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

የኢኒሼቲቩ የልማት አጋር አገሮችን በመወከል ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የኔዘርላንደስ አምባሳደር ሃንስ ብላንክንበርግ በበኩላቸው ለተፋሰሱ አገሮች ዘላቂ ልማት መረጋገጥ ጠንካራ ትብብር መፍጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

የተፋሰሱ አገሮች መንግሥታትም በዚህ ረገድ ፖለቲካዊ ቁርጠኛነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የተፋሰሱ አገሮች በናይል ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀም ዙሪያ የሚፈጥሩትን ትብብር ለመደገፍ አገራቸውን ጨምሮ የአጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዓመታዊውን የናይል ቀን የነጭ ዓባይ መነሻ በሆነችው የዩጋንዳዋ ጂንጃ ከተማ የተፋሰሱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች በተገኙበት በድምቀት ዛሬ ተከብሯል፡፡

የመጀመሪያው የናይል ቀን በሩዋንዳ ኪጋሊ የተከበረ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ መከበሩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ አባል አገሮች ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛንያና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሲሆኑ፣ ኤርትራ ታዛቢ መሆኗን የዘገበው ኢዜአ ነው፡