የውጭ መገናኛ ብዙሃን ስለ ጋምቤላ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም የሚያናፍሱት ዘገባ የተሳሳተና ከእውነታ ጋር የተቃረነ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2004 (ዋኢማ) –  የውጭ መገናኛ ብዙሃን በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ያለውን የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም በተመለከተ የሚያናፍሱት ዘገባ የተሳሳተና ከእውነታው ጋር ፍጹም የተቃረነ መሆኑን አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ገለጹ።

አፈ ጉባኤው ከአውሮፓ ህብረት ጥምር ፓርላማ ተባባሪ ሊቀመንበር ሉዊስ ሚሼል ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በምእራብ ኢትዮጵያ በተለይም በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ያለውን የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም በግዳጅ የተከናወነ አስመስለው የተሳሳቱ ዘገባዎችን ያሰራጫሉ፡፡ ዘገባውም በተጨባጭ ካለው እውነታ ጋር ፍጹም የተራራቀ ነው ብለዋል።

የመንደር ማሰባሰቡ ፕሮግራም በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎና መልካም ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተና አንድም ግለሰብ ቢሆን በፕሮግራሙ ውስጥ ያለ ፈቃዱ እንዲካተት የማይፈቀድ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

“ሰዎች በኃይል እየተፈናቀሉ መሬታቸው ግን ያለ አግባብ ለውጭ ባለሃብቶች እየተሰጠ ነው” በሚል አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች ያሰራጨው በስህተት የተሞላ ሪፖርት የአለም አቀፉን ማህብረሰብ የሚያደናገርና ትክክለኛውን ስዕል የማይሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ገና ያልተጠቀመችበት እጅግ ሰፊ ለም መሬት ያላት መሆኗን ለልኡካን ቡድኑ ያብራሩት አፈጉባኤው መንግስት አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው በግድ ሊያፈናቅል ቀርቶ ሰዎች ያልሰፈሩባቸው ሰፋፊ ለም መሬቶች እንኳን ገና ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የመንግስትን ፍላጎት ያህል ብዙ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በግብርናው መስክ እንዳልተሰማሩም ጠቅሰዋል።

በመንደር ማሰባሰቡ ፕሮግራም ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች አስፈላጊ የሆኑ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት እየተሟሉ እንደሆኑም ተናግረዋል።

የልኡካን ቡድኑ አባላት ፍላጎት ካላቸው ወደ አካባቢው በመሄድ እውነታውን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚችሉ መግለጻችውን ውይይቱን የተከታተሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት ጥምር ፓርላማ ተባባሪ ሊቀመንበር ሉዊስ ሚሼል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት ፓርላማዎች መካከል አልፎ አልፎ የማያግባቡ ጉዳዮች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ የትብብር ግንኙነት በትክክለኛው መስመር ላይ ይገኛል።

ሚስተር ሚሼል ሁልጊዜም ቢሆን በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እንደሚከተታሉ ገልጸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የተደቀነባትን ፈተናዎች ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት የአውሮፓ ፓርላማ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚካሄደው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች እንደሆነ የገለጹት ሉዊስ ሚሼል ኢትዮጵያ በአካባቢው እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ አገር መሆኗን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረትና የኢትዮጵያ ፓርላማ ወደፊት በተቀናጀ መልኩ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች እና የልምድ ልውውጥ በሚደረግባቸው አጀንዳዎች ዙሪያም መክረዋል።

ሁለቱ ፓርላማዎች በዴሞክራሲ፣ በአቅም ግንባታና በሌሎችም አለም አቀፍና አህጉራዊ ጉዳዮችን በተመለከተም መወያየታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።