ኮሚሽኑ በሙሰኞች የተመዘበረ ገንዘብ፣ ሃብትና ንብረቶች በፍርድ ቤት እንዲታገድና እንዲመለስ አደረገ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2004 (ዋኢማ) – የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙሰኞች የተመዘበረ ገንዘብ፣ ሃብትና ንብረቶች በፍርድ ቤት እንዲታገድና እንዲመለስ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የሥነ ምግባር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ በግማሽ በጀት ዓመት ካሳገዳቸው ንብረቶች መካከል ከ19 ሺህ በላይ ካሬ ሜትር መሬት፣ ዘጠኝ መኪኖች፣ አስራ ስድስት መኖሪያ ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪም አንድ ሆቴል፣ 172 ሄክታር የእርሻ ኢንቨስትመንት፣ አንድ የንግድ መጋዘንና በተጠርጣሪዎች ስም በባንክ የሚገኝ ከ725 ሺህ 155 ብር በላይ ይገኝበታል ብለዋል፡፡

በሙሰኞቹ ተመዝብረው ከነበሩት መካከል በፍርድ ቤት ውሳኔ ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ተመላሽ መደረጋቸውንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

ወደ መንግስት እንዲመለሱ የተደረጉ ንብረቶች ወደፊት እንደ ውሳኔው እርምጃ የሚወሰድባቸው ነገር ግን እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡና እንዳይባክኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ከተመለሱት ንብረቶች መካከል ስድስት መኖሪያ ቤቶች፣ 18 ተሽከርካሪዎች፣ ከ86 ሺህ በላይ ካሬ ሜትር መሬት፣ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እና ሁለት ሞተር ብስክሌቶች ይገኙበታል፡፡

ኮሚሽኑ መደበኛ በሆነው የሙስና መከላከል ሥራ በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች የአሠራር ሥርዓት ከሚከናወኑት ተግባራት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ጥናት አካሂዷል፡፡

ከዘጠኝ ተቋማት ጋር በሚደረግ ውይይት መሰረት ስምምነት የተደረሰበት የአሠራር ማሻሻያ ሃሳብ ዝርዝር መርሃ ግብር ተቀርፆ ለተግባራዊነቱ ለየመስሪያ ቤቱ ይላካል፤ ለአፈፃፀሙ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በተለያዩ ተቋማት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ ናቸው ባላቸው አርባ ሶሰት ተግባራት ላይ ጥናት የጀመረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ሀያ ሶስት የአሰራር ጥናቶች ተጠናቀው ለተቋሞች መላኩንም ጠቁመዋል፡፡

በሃያዎቹ ላይ ደግሞ መረጃ የማሰባሰብ፣ የማጠናቀርና ረቂቅ ሪፖርት የማዘጋጀት ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በእነዚህ ተቋማት አስቿኳይ የሙስና መከላከል ስራዎች ተጠናቋል፡፡

በተቋማቱ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት አኳያ፣ በስልክና በአካል ከ150 በላይ ለሚሆኑ የምክር አገልግሎት መሰጠቱንም አቶ ብርሃኑ መግለፃቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡